ኬንያ ለኡጋንዳ የባህር በር እንደምትሰጥ አስታወቀች

ከአንድ ሳምንት በፊት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ሀገራቸው የባህር በር ካላገኘች ከኬንያ ጋር ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ኬንያ ለኡጋንዳ ጥያቄ በይፋ መልካም ምላሽ ሰጥታለች።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጎረቤቷ ለሆነችው ኡጋንዳ የባሕር በር እንደምትሠጥ አስታውቀዋል።

ኡጋንዳ በኬንያ በኩል በነዳጅ ቧንቧ፣ በመንገድ እና በባቡር ሐዲድ አማካኝነት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የባሕር በር እንድታገኝ እናደርጋለን ብለዋል ፕሬዝዳንት ሩቶ።

ኬንያ ለኡጋንዳ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዋን የሚያስተዳድረውን መንግሥታዊ ኩባንያ ከኡጋንዳ ጋር በጋራ ባለቤትነት ለመያዝ ፍቃደኛ መኾኗንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ኬንያ በቻይና እርዳታ የተዘረጋውን የባቡር ሐዲዷን በቅርቡ እስከ ኡጋንዳ መዲና ካምፓላ ከተማ ድረስ እንደምትዘጋም በፕሬዝዳንቷ በኩል አስታውቃለች።

ሌላኛዋ ወደብ አልባ ሀገር ኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ እንደሚያስፈልጋት በይፋ ስትገልጽ ከዓመት በላይ ሆኗታል።

ኢትዮጽያ ከራስገዟ ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ለማግኘት የጀመረችው ጥረት መክሸፉን ተከትሎ የአሰብ ወደብ እንደሚገባት በመግለጽ ላይ ናት።

አሰብ ወደብ በኤርትራ በግፍ አደተወሰደባት የምትገልጸው ኢትዮጵያ ከአስመራ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአንድ ወር በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት “አሰብ ወደብ ከኢትዮጵያ በግፍ መወሰዱን፣ ወደቡ በኤርትራ እንዲወሰድ የተላለፈ ምንም አይነት ውሳኔ የለም” ማለታቸው ይታወሳል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ሲባል ኤርትራ በትጥቅ ትግል ያሳካችውን ነጻነት ለመቀልበስ ፍላጎት አላት ሲሉ ገልጸዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *