ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከፓርላማ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በአንድ ጀምበር የመጣ ሳይሆን ቀስ በቀስ በሂደት መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከስድስት ዓመት በፊት የባህር ሀይሏን እንዳቋቋመች የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህ ሀይል የተቋቋመው በሀገር ውስጥ ብቻ እንዲገታ በማሰብ አልነበረም አሰብ ወደብን ከኤርትራ እንደምንረከብ በማመን ነበር ብለዋል።
“ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተስማምተን ከዚህ ወደ አሰብ የሚወስደውን መንገድ ጠግነናል ፣እንከፍታለን ብለን ጠግነናል፣ መንገዱን ከጠገንን በኋላ ግን ችግር አለብን አሰብ ወደብ ተዳክሟል አሉን። አንዳንድ ሰው ከኤርትራ ጋር የገባንበት አለመግባባት በአንድ ምሽት የመጣ ይመስለዋል እንደዛ አይደለም ታሪኩን ስለማንናገር ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ።
ወደ አሰብ መንገድ ጠግነን ከጨረስን በኃላ ‘ ፖርቱ ችግር አለበት ‘ ሲሉ የሁለታችንም የጋራ ወዳጅ ከሆነ ሀገር ጀነሬተር እና ክሬን በእርዳታ ወደ ኤርትራ እንዲመጣ አድርገን አሰብ ወደብ ሲደርስ የኤርትራ መንግስት ‘ አልፈልግም ‘ ብሎ መለሰ ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም መንገድ ከጠገን እና ጀነሬተር ከመትከል በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ሀይል እናስገባላችሁ ብለን ብንጠይቅም እናስብበት ተብለናል ብለዋል።
በኤርትራ በኩል በግልጽ ባላወቅነው መንገድ ለዚያ ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ብዙ ዝግጁ ካለመሆናቸው ባለፈ የከፈትናቸውን ድንበሮች በሰሜን በኩል ወዲያው መዘጋታቸውንም ተናግረዋል።
ከኤርትራ ህዝብ ጋር መስራት እና መተባበር ፍላጎታችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ውጊያ የማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው እና ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል ።
ከኤርትራ ጋር ያለውን አለመግባባት እንዲያሸማግሏቸው ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለራሽያ፣ ለአውሮፓ ፣ለአፍሪካ ህብረት መናገራቸውንም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ገልጸዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጠቃሚነት ጉዳይ አይቀሬ ስለሆነ ቅድሚያ የምንሰጠው ሰላምና ንግግር ስለሆነ እባካችሁ ሸምግሉን እና መፍትሄ አምጡልን ብለን የጠየቅናቸው ሀገራት ሰላም ያስፈልጋል እያሉ የሚያዘናጉ ከሆነ እንደማያዋጣ ጠቅሰዋል።
በ30 አመት ርብርብ ቀይ ባህርን ኢትዮጰያ አጥታለች ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ግን 30 አመት ይፈጅብናል ብዬ አላስብም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ቀይ ባህርን ኢትዮጵያ ለምን እንዳጣች ምንም አይነት የህዝብም ሆነ የመንግስት ውሳኔ እንዳልነበር ገልጸው የወደብ ጉዳይ የህልውናቸውን ጉዳይ ነው ብለዋል።