ታርኮ አቪዬሽን ከፖርቱ ሱዳን- አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ

ታርኮ አቪዬሽን የተሰኘው ተቋም ከሱዳን ጊዜያዊ የአስተዳድር ዋና ከተማ ከሆነችው ፖርቱ ሱዳን ወደ አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል።

የቀጥታ በረራው ከጥቅምት 20 ጀምሮ እንደሚጀመር የኩባንያው ክልላዊ ስራ አስኪያጅ ኦማር አህመድ እድሪስ ገልጸዋል።

እንደ ኦማር አህመድ ገለጻ የታርኮ አቪዬሽን ቀጥታ በረራ መጀመር የኩባንያው አድማሱን ለማስፋት የያዘው እቅድ ነው።

የቀጥታ በረራው በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን የንግድ ትብብር ከመጨመሩ ባለፈ ለነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች እና ተጓዦችም ልዩ እድል እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ታርኮ አቪዬሽን ከፖርት ሱዳን- አስመራ የቀጥታ በረራ ያለው ሲሆን አዲሱ ከፖርት ሱዳን- አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ የኩባንያውን ተደራሽነት ያሰፈዋልም ተብሏል።

ስራ አስኪያጁ አክለውም ታርኮ አቪዬሽን ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እና ደህንነት ዋነኛ ትኩረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ታርኮ አቪዬሽን መሰረቱን ሱዳን በማድረግ በአፍሪካ እና የአረብ ሀገራት መንገደኞችን በማጓጓዝ ልምድ ያለው ተቋም ነው።

አዲሱ ከፖርት ሱዳን- አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ የሁለቱን ሀገራት ቱሪዝም እንደሚያነቃቃው ይጠበቃል።

በሱዳን ጦር እና ፈጣን ሀይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱን ሊይዝ ጥቂት ወራት ይቀረዋል።

በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለሞት እና አካል ጉዳት መዳረጋቸውን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *