ኢትዮጵያ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር የሚያመርት የጋዝ ማጣሪያ አስመረቀች

በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር የሚያመርተው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀናል ብለዋል።

በተመሳሳይ በዓመት 1 ነጥብ 33 ቢሊየን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን የነዳጅ ማጣሪያ ስራ ማስጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡

ማጣሪያው ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት ባሻገር በኃይል ማመንጫ ዘርፉም 1 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ፕሮጀክቱ የጋዝ ማምረቻ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት በማቅረብ ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረታችን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ማጣሪያው ለኃይል ማመንጫ እና የክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብም አብራርተዋል።

በሶማሌ ክልል የተጀመሩት ከተያያዥ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጋር በአጠቃላይ ወደ 10 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትናንትናው ዕለት በሶማሊ ክልል ጎዴ ዞን የአፈር ማዳበሪያ እና ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር ይገነባል ተብሏል።

ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ ደግሞ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካን እንደሚገነባ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ከሂላል የነዳጅ ስፍራ ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራትና በማጠራቀም በአመት 3.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም አለውም ተብሏል።

በሌላ በኩልም የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣት እና 108 ኪሎሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በአመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ ያቀርባል።

ፋብሪካው በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል መሆኑንም በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርት ሲሆን በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል።

ኢትዮጵያ በዓመት ለአፈር ማዳበሪያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የምታወጣ ሲሆን ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ለመገንባት ከ10 ዓመት በፊት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን እውን መሆን አልቻለም፡፡

የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆነው ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያለው ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ እና የስኳር ፋብሪካዎችን የመገንባት እቅድ እንዳለው ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ፋብሪካ ወጪ ለማስቀረት በሀገር ውስጥ ፋብሪካ ለመገንባት ብዙ ጥረቶችን አድርጋ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሳይሳካ ቆይቷል፡፡
ለአብነትም ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ከ10 ዓመት በፊት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ፋብሪካው በሙስና እና ሌሎች ምክንያች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

እንዲሁም ከሞሮኮው ኦሲፒ ኩባንያ በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ለመገንባት ከአምስት ዓመት በፊት ስምምነት የተደረገ ቢሆንም ፋብሪካው እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *