ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ በየዓመቱ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ እንደምታደርግ ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ መጋቢት 2፣ 2018 በሰጡት መግለጫ በእስራኤል-አሜሪካ እና ኢራን መካከል በተጀመረው ጦርነት ምክንያት ለነዳጅ ድጎማ የሚያወጣው ወጪ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ ይህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያ አንድ ሊትር ቤንዚን በ129 ብር ለተጠቃሚዎች ስታቀርብ የነበረ ሲሆን ድጎማው ቢቀር ግን የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ዋጋ 157 ብር ይሆን ነበር፡፡ እንዲሁም ነጭ ናፍጣ 129 ነበር በሊትር ሲሸጥ ነበር የተባለ ሲሆን ድጎማው ቢነሳ 182 ነጥብ 8 ብር መሸጥ ነበረበት ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያ ቤንዚን የ28 ነጥብ 7 ብር እንዲሁም ነጭ ናፍታ 53 ነጥብ 7 ብር በሊትር ስትደጉም እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት በተደረገው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማሻሻያ መሰረት ደግሞ አንድ ሊትር ቤንዚን 132 ነጥብ 18 ብር ነጭ ናፍታ ደግሞ 139 ነጥብ 8 ብር እንዲሆን መደረጉ ሲገለጽ አሁን ባለው ዓለም ነዳጅ ገበያ መሰረትም የቤንዚን መሸጫ ዋጋ የ73 ብር እንዲሁም የናፍጣ ደግሞ የ98 ብር ድጎማ እንደተደረገ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጻ ኢትዮጵያ የነዳጅ ድጎማ ባታደርግ በዓለም አቀፉ የነዳጅ ገበያ መሰረት የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ዋጋ 205 ነጥብ 74 ብር እንዲሁም የነጭ ናፍጣ ደግሞ 238 ነጥብ 13 ብር መሆን ነበረበት፡፡
ለነዳጅ ድጎማ የሚደረገው የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል እና የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተካከል ነው የሚሉት ሚኒስትሩ በድጎማ የሚገዛው ነዳጅ ከተቀመጠው የግብይት ሰንሰለት ውጪ እና ከተቀመጠለት ዋጋ በላይ እየተሸጠ እንደሆነ መንግስት በጥናት አረጋግጧልም ብለዋል፡፡
መንግስት በጦርነቱ ምክንያት የዓለም ነዳጅ አቅርቦት በመስተጓጎሉ የነዳጅ ቀውሱ ወደ ሀገራችን እንዳይመጣ የተዘጋውን የሆርሙዝ ንግድ መስተጓጎል ጉዳት ለመቀነስ አማራጭ የንግድ መስመሮችን ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና ሚኒስትሩ መንገስት እያደጋቸው ስላሉ አማራጭ የንግድ መስመሮች ዙሪያ ሚኒስትሩ አልጠቀሱም፡፡
አቶ አህመድ አክለውም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየቀረበ ያለውን ሀብት በተቀመጠው ህጋዊ የግብይት ሰንሰለት እንዲገበያይ አሳስበዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መቼ እንደሚቆም አለመታወቁን ያነሱት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ በቁጠባ እና በሀላፊነት መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መንግስት በህገወጥ የነዳጅ ግብይት የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡