በሶማሊ ክልል ጎዴ የአፈር ማዳበሪያ እና ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ተጀመረ

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የዩሪያ ማዳበሪያ እና ጌዴ ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታን አስጀምረዋል።

የዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር ይገነባል ተብሏል።

ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ ደግሞ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካን እንደሚገነባ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ከሂላል የነዳጅ ስፍራ ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራትና በማጠራቀም በአመት 3.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም አለውም ተብሏል።

በሌላ በኩልም የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣት እና 108 ኪሎሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በአመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ ያቀርባል።

ከአንድ ወር በፊት አሊኮ ዳንጎቴ ግሩፕ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ፕሮጀክቱ በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል መሆኑንም በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርት ሲሆን፤ “ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ ያደርጋታል” ተብሏል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል ይፈጥራል” ያሉ ሲሆን “ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል። ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታል” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም፤ “በመላው አህጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት ለአፈር ማዳበሪያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የምታወጣ ሲሆን ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ለመገንባት ከ10 ዓመት በፊት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን እውን መሆን አልቻለም፡፡

የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆነው ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያለው ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ እና የስኳር ፋብሪካዎችን የመገንባት እቅድ እንዳለው ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ፋብሪካ ወጪ ለማስቀረት በሀገር ውስጥ ፋብሪካ ለመገንባት ብዙ ጥረቶችን አድርጋ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሳይሳካ ቆይቷል፡፡
ለአብነትም ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ከ10 ዓመት በፊት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ፋብሪካው በሙስና እና ሌሎች ምክንያች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

እንዲሁም ከሞሮኮው ኦሲፒ ኩባንያ በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ለመገንባት ከአምስት ዓመት በፊት ስምምነት የተደረገ ቢሆንም ፋብሪካው እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *