ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ከሸጠችው ኤሌክትሪክ ከ118 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ

በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 118 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኤሌክትሪክ ሃይል ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይም ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እየሸጠች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት 25 ሺሕ በላይ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 29 ሺሕ በላይ ጊጋ ዋት ሰዓት ማመንጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከተመረተው ኃይል ውስጥም ለኬንያ 85 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ለማከናወን ታቅዶ 86 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በቅደም ተከተል 30 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር እና 900 ሺሕ ዶላር መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ከሦስቱ ሀገራት በተጨማሪ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለጎረቤት ሀገራቱ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭም በአጠቃላይ 118 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ካመረተው ሃይል ውስጥ 7 በመቶውን ወደ ውጪ በመላክ ከተቋሙ አጠቃላይ ገቢ 20 በመቶ የሚሆነውን መሸፈን ስለመቻሉም ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ለሱዳን ከፍተኛ ሀይል ከምትሸጥባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ባጋጠመው የእርስ በርስ ጦርነት ይላክ ከነበረው ሀይል 80 በመቶው ቀንሷል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በ5 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ እንደሚመረቅ ይጠበቃል።

ከ5 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለህ የህዳሴው ግድብ በሀይል የማመንጨት አቅሙ ከአፍሪካ ትልቁ ነው።

መንግሥት ይህን ግድብ ለመመረቅ እንግዶችን በመጋበዝ ላይ ሲሆን የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ግብዣውን እንደተቀበሉ ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታን ሲቃወሙ የነበሩት ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ምረቃ በዓል ላይ እንዲገኙ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ተጋብዘዋል።

የህዳሴው ግድብ በሙሉ አቅሙ ተመርቆ ሀይል ማመንጨት ሲጀምር የኢትዮጵያን የሀይል ማምረት አቅም ከዕጥፍ በላይ ያሳድገዋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *