የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ28 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበት ገለጸ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በተቋሙ የበጀት አመት አፈጻጸም ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከነዚህም ጥያቄዎች መካከል ከበረራ ትኬቶች ውድነት ጋር እና አየር መንገዱ በኤርትራ ከተያዘበት ገንዘብ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሲሆን ዋና ስራ አስፈጻሚው ምላሽ ሰጥተውበታል።

ከሀገር ውስጥ በረራ ጋር በተያያዘ የ28 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

“የዓለም አቀፍ በረራዎች ትኬት ኮምፒውተር ውስጥ በዶላር ነው የተጻፈው ሰው ትኬት ሲገዛ በእለታዊ የዶላር ምንዛሬ ተመን ነው ይህንን ምንም ልናደርግ አንችልም።

የሃገር ውስጥ በረራ ግን በብር ነው የተጻፈው ባለፈው አመት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወቅት አልጨመርንም የዶላር ምንዛሬ ዋጋው ሁለት እጥፍ ነው ያደገው በሃገር ውስጥ በረራ ክፍያ ላይ ግን ጥቃቅን ማሻሻያ ብቻ ነው ያደረግነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 28 ሚሊየን ዶላር በሃገር ውስጥ በረራ ከስሯል ምክንያቱም አውሮፕላኖች የሚገዙት በዶላር ነው ፣ የተከራየነውን አውሮፕላን የምንከፍለው በዶላር ነው፣ የመለዋወጫ እቃ የምንገዛው በዶላር ነው፣ የነዳጅ ዋጋ አድጓል።

ነገር ግን ይህ ቀጣይነት ሊኖረው አይችልም ፣አየር መንገዱ እየከሰረ አይቀጥልም ያለፈውን አንድ አመት ለማረጋጋት ብለን ይዘነው ቆይተናል ቀስ እያለን ግን ወጪ ወደ መሸፈን እና ከፍ ወደ ማድረግ ደረጃ መሄዱ አይቀርም ብለዋል።

የበአላት ወቅት የበረራ ክፍያ ዋጋ የሚጨምረው አውሮፕላኑ ባዶውን እንዳይመጣ ወጪውን ለመሸፈን ሲባል የደርሶ መልስ ዋጋውን ባይሆንም ክፍያው እንዲጨምር እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በመደበኛ በረራ ወቅት አውሮፕላኑ ሲሄድም ሲመጣም ተጓዦችን ጭኖ ነው። በበዓላት ወቅት ግን ለምሳሌ የቁልቢ ገብርኤልን በአል ብንመለከት በአሉ ሲደርስ አንድ ወይም ሁለት ቀን ሲቀረው ብዙ ተጓዥ ወደ በአሉ ቦታ የሚሄድ እናገኛለን ሲመለስ አውሮፕላኑ ባዶውን ነው የሚመለሰው እንደዚህ ሲሆን ወጪውን ለመሸፈን ስንል ሙሉ ለሙሉ የደርሶ መልስ ዋጋውን ባይሆንም ቢያንስ ከመሄጃው በላይ ዋጋው ይጨምራል።

በአሉን አክብረው ለሚመለሱት ደግሞ አውሮፕላኑን ከዚህ ባዶውን ነው የምንልከው ሰው ለማምጣት ስንሄድ በቀን እስከ ሃያ በረራ እናከናውናለን ስሄድ ባዶውን ሄዶ ፣ሲመለስ ነው የሚጭነው ይህንን ህዝቡ እንዲረዳው እንፈልጋለን ” ብለዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከአንድ ዓመት በፊት በሰጡት መግለጫ አየር መንገዱ በኤርትራ ባንክ ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዳይችል እንደታገደ መግለጻቸው ይታወሳል።

በወቅቱ በሐምሌ ወር የኤርትራው ባንክ አየር መንገዱ በኤርትራ ያለውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይወስድ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ስለመታገዱ ከባንኩ መስማታቸውን የተናገሩት አቶ መስፍን፤ ” ገንዘብ ማውጣት አልቻልንም ባንኩ እንዳታወጡ ታግዳችኋል አለን፣ ባንኩ የሚለው የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ከአገር እንዳያወጣ ከልክሏል ነው ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ወደ ኤርትራ በረራ አቁመናል በኤርትራ አየር ክልል ግን እየበረርን ነው የሃገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በዚህ ጉዳይ ምንም ችግር የለበትም ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም ” ፈቅደውልናል ከኢትዮጵያ ስንወጣም ወደ ኢትዮጵያ ስንገባም የኤርትራን የአየር ክልል አንዳንዴ ጊዜ የሱዳንን አየር ክልል እየተጠቀምን እየሰራን ነው ” ብለዋል።

የተያዘውን ገንዘብ በሚመለከት ግን ” ገንዘባችን አሁንም እንደተያዘ ነው በፍርድ ቤት ለማስለቀቅ ሙከራ አድርገን ነበር ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ገንዘባችንን ሊያስለቅቅልን አልቻለም የፖለቲካ ውሳኔ ይፈልጋል” ሲሉም አክለዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት በዓመቱ 6 ዓለም አቀፍ ጣቢያዎች መክፈት የቻለው አየር መንገዱ 13 የተለያዩ አውሮፕላኖች ወደ ስራ አስገብቷል።

በ2017 በጀት ዓመት 19 ሚሊየን መንገደኞችን አየር መንገዱ ማጓጓዝ ሲችል በጭነት አገልግሎት  ደግሞ 785 ሺህ 323 ቶን በላይ ካርጎ እንዳጓጓዘም ጨምረው አስታውቀዋል።

ከመንገደኞችና ዕቃ ጭነት አገልግሎትም 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አስታውቀዋል።

አሁን ላይ የአየር መንገዱ የሀገር ውስጥ በረራ መዳረሻዎች 21 መሆናቸውን እና  በቅርቡ የሚጠናቀቁ የ5 ኤርፖርቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *