በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች እንዲሰሩ ተፈቀደ

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከዛሬ ጀምሮ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሆነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት የሚያደርግ አዲስ መመሪያን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ይህ እርምጃ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ ሲደረግ የቆየው ጥረት የመጨረሻው ምዕራፍ ተደርጎ እንደሚወሰዱ ተገልጿል።

መመሪያ ቁጥር SBB/94/2025 ባለፉት አንድ ዓመት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተደረጉ ሰፊ ውይይቶች እና ምክክሮች ግብዓት ተደርጎበት የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

ይህ መመሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፀደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ መሰረት የወጣ ሲሆን፣ የሚያስፈልገውን የሕግ ማዕቀፍ ማሟላቱ ተገልጿል።

ይህ አዲሱ የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ባለሀብቶች፣ ባንኮችን እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ባለሀብቶችን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ የባንክ ሥርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ ያስችላል ተብሏል።

ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣዉ መግለጫ መመሪያው የውጭ ተዋናዮች የባንክ ዘርፉን እንዲቀላቀሉባቸው በርካታ መንገዶችን ያቀርባል፤ ከእነዚህም መካከል ቅርንጫፍ ባንኮችን፣ የውጭ ባንክ ቅርንጫፎችን ወይም የወኪል ቢሮዎችን ማቋቋም ይገኙበታል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት መሆኑን የገለፀ ሲሆን የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶችም ማመልከቻዎቻቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት እንደታቀደ ገልጾ ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ በወቅቱ ገመናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ከአንድ ወር በፊት በተካሄደ የባንክ ኤክስፖ ላይ ባደረጉት ንግግር የ2025 ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ብለው ነበር።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *