ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ሳምንት ሀገራቸው አሜሪካ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተያየት ውድቅ አድርጓል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ ፕሬዝዳንቱ ቱርዝ ሶሻል ተብሎ በሚጠራው የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ዩናይትድ ስቴትስ የህዳሴ ግድብን በገንዘብ ደግፋለች ማለታቸውን “መሠረተ ቢስ” ብለውታል።
ኃላፊው “ህዳሴ ግድብ ከ20ዐ3 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት፣ ጉልበት፣ እውቀትና በኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ ያለ ነው” ሲሉ አፅዕኖት ሰጥተዋል።
አክለውም የአሜሪካው መሪ ንግግር ከዓለም አቀፋ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከ15 ዓመት በፊት ለግንባታው መሰረት ድንጋይ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ ግንባታው 97.6 በመቶ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናግሯል፡፡
ህዝቡ እስካሁን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ በበጎ ፈቃደኝነት ያዋጣ ሲሆን በዚህ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴው ግድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።
በሀይል ማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው የሕዳሴው ግድብ በአጠቃላይ ሀይል የሚያመነጩ ሰባት ዩኒቶች ይኖሩታል ተብሏል።
ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በአባይ (ናይል) ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እየተቃወሙ ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
ግብጽ ለሶስትዮሽ ድርደሩ ኢትዮጵያን ተጠያቂ ስታደርግ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ውሎች እንዲቀጥሉ ስለምትፈልግ እንዳልተሳካ አሳውቃለች፡፡