የአልኮል ምርቶችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ማስተዋወቅን በከፊል የሚከለክል የህግ ረቂቅ ተዘጋጅቷል
የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለሰልጣን የአልኮል ምርቶችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ማስተዋወቅን በከፊል የሚከለክል የህግ ረቂቅ አዘጋጅቶ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የአልኮል ምርቶችን እንደ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ባሉ መገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅ በህግ ማገዷ ይታወቃል።
የአልኮል አምራች ተቋማት በአሁን ሰዓት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም፤ ምርታቸውን እያስተዋቁ እና ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች እየደረሱ ነው ተብሏል።
ከእነዚህ መካከልም የማህበራዊ ሚዲያ በብዛትና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ እንደሆነ ተነግሯል።
ይህንን እየተስፋፋ የመጣው በማህበራዊ ሚዲያ የአልኮል ማስታወቂያን በተቻለ መጠን ለመገደብ ታስቦ፤ የህግ ማዕቀፍ ተሰናድቶ በሒደት ላይ እንደሚኝ በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የህግ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ፍሬሰላም ዮሴፍ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የተሰናዳው ረቂቅ ህግ ወደ ጤና ሚኒስቴር መላኩንም ስራ አስፈፃሚዋ ጨምረው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በፊት የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎችን በብሮድካስት ሚዲያዎች እንዳይተላለፉ እገዳ ጥላለች።
እንደ ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ጥናት ከሆነ ኢትዮጵያ የአልኮል መጠጥ ዝቅተኛ ከሆኑባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን አንድ ሰው በአማካኝ 3 ሊትር አልኮል ይጠጣል።
በኢትዮጵያ 12 የቢራ አይነቶች ያሉ ሲሆን ፋብሪካዎቹ በስድስት ኩባንያዎች ባለቤትነት ሲተዳደሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ደግሞ የመጀመሪያው ቢራ ምርት ነው።