የብሪክስ አባል ሀገራት 65 በመቶ ግብይታቸውን ከዶላር ውጭ ማድረጋቸው ተገለጸ

ኢትዮጵያ አባል በሆነችው ብሪክስ የንግድ ልውውጥ ከዶላር እየራቀ 65 በመቶ በብሔራዊ ገንዘቦች እየተከናወነ ነው ተብሏል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል የሆኑት የብሪክስ አገራት (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች) በንግድ ልውውጣቸው ከአሜሪካ ዶላር እየራቁ ሲሆን ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ንግድ አሁን በአባል አገራቱ ብሔራዊ ገንዘቦች እየተከናወነ ነው።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በብራዚል በተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት መግለጫ ሲሆን፣ ይህ አዝማሚያ ቡድኑ በፋይናንስ ረገድ ያለውን ነፃነት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ላቭሮቭ አክለውም “BRICS Pay” የተባለ ገለልተኛ የክፍያ ስርዓት ለመመስረት የሚደረጉ ውይይቶች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የBRICS የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች በካዛን ጉባኤ በተሰጠው መመሪያ መሠረት በጋራ ንግድ ውስጥ ብሔራዊ ገንዘቦችን በንቃት ለመጠቀም ተስማምተዋል።

ይህ እርምጃ ብሪክስ በምዕራባውያን የገንዘብ ስርዓቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያደርገውን የጋራ ጥረት ያሳያል ተብሏል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ለአዲሱ የልማት ባንክ (ቀደም ሲል የብሪክስ ልማት ባንክ በመባል ይታወቅ የነበረው) በይፋ አባልነት ለመቀላቀል ማመልከቻ ማስገባቷና የዚህ ሂደት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልፃ እንደነበር ይታወሳል።

ባሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ለምታደርጋቸው የንግድ ግብይቶች በየራሳቸው መገበያያ ማለትም ከዶላር ውጪ ለመገበያየት መስማማታቸው ይታወሳል።

ሩሲያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ቱኒዝያ፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና፣ ናይጀሪያ እና ሌሎችም ሀገራት ጋር ከዶላር ውጭ ግብይት እንዲፈጽሙ ፈቃድ ሰጥታለች።

ይህ በዚህ እንዳለ ሁለቱ የብሪክስ አባል ሀገራት የሆኑት ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት መስማማታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዶላር ውጭ የሚገበያዩ ሀገራት ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉ መዛታቸው አይዘነጋም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *