በኮንትሮባንድ ንግድ የተሳተፋ ከ50 በላይ የቡና ላኪዎች እገዳ ተጣሎባቸዋል።
የቡና ምርት ለኮንትሮባንድና ለተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶች እየተጋለጠ በመሆኑ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት እየጎዳው ይገኛል ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር እንደተናገሩት ቡናን ለአልባሌ ነገር እንዳይውል ለማድረግ በሶፍት ዌር አማካኝነት እያንዳንዱ ምርት ከመነሻ እስከ መድረሻ መድረሱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህም በተለይም ቡናን በአግባቡ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀው ምርቱን ለኮንትሮባንድ ንግድ የሚያውሉ አካላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት ቡናን ወደ ትክክለኛው መዳረሻ እንዲደርስ ባላደረጉት አካላት ላይ ከአስተዳደራዊ እርምጃ አንስቶ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል።
በህገወጥ መልኩ ቡናን እየደበቁ ያሉትን በተመለከተ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከብሄራዊ መረጃ ደህንነት እና ከህግ አካላት ጋር በመሆን የቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም ምርቱን በቁጥጥር ስር ማዋልና መያዝ እንደተቻለ አብራርተዋል።
ከጉዳዮ ጋር በተያያዘ 14 የቡና ላኪዎች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ጠቅሰው ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል በማለት አቶ ሻፊ ጨምረው ተናግረዋል።
ቡናን በህገወጥ ተግባር ለማሸሽ መሞከር የሀገርንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚጎዳ እንደመሆኑ ለጉዳዮ መፍትሄ ለማምጣት አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች መባሉ ይታወሳል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፋት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና፣ ወርቅ እና ሌሎች ምርቶች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
ከተገኘው ገቢ ውስጥም ወርቅ 1.8 ቢሊዮን ዶላር፣ ቡና 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ከቡና ንግድ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።
በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ቡና አምራች ገበሬዎች ያሉ ሲሆን ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በቡና ንግድ ላይ የተመሰረተ ነው።