የአማራ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ሲያካሄዱት የቆየው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቋል፡፡
የአማራ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ካለፈው እሁድ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲያካሄዱት የቆየው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መጠናቁን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የማህበረሰብ ተወካዮቹ፤ በመጪዎቹ ቀናት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ የምክክር ሂደት የሚሳተፉ 270 ወኪሎቻቸውንም መርጠዋል።
በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ከ263 ወረዳዎች የተመረጡ ከ4,500 በላይ የሚሆኑት የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
አስር የማህበረሰብ ክፍሎችን የወከሉት እነዚህ የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች፤ በባህርዳር ከተማ በነበራቸው ቆይታ ከዘጠኝ እስከ 12 አባላት በሚገኙባቸው ቡድኖች ተከፋፍለው በአበይት ክልላዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማርያም፤ የማህበረሰቡ ተወካዮች ያቀርቧቸው የነበሩ አጀንዳዎች “በትናንሽ ነገሮች ላይ ያተኮሩ አልነበሩም፣ትላልቅ አጀንዳዎች፤ ለሀገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን ነበር ያነሱት” ሲሉ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ተወካዮቹን ምክክር “በጣም የተሳካ” እና “በጣም ውጤታማ” ሲሉ የገለጹት አቶ መላኩ፤ ሂደቱን “አሳታፊ፣ አካታች፣ ግልጽነት የተሞላበት እና በነጻነት የተካሄደ ነበር” ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ “ዜጎቻችን የት ደረጃ እንደደረሱ ማየት የቻልንበት ነው” ሲሉ የተደመጡት ኮሚሽነሩ፤ “ትምህርት የተማርንበት ሂደት ነው ማለት እንችላለን” በማለት ያን ያሉበትን ምክንያት አብራርተዋል።
“ከዚህ የምክክር ሂደት አማራ ክልል ያየነው ነገር፤ ትምህርት ያገኘንበት፣ የዜጎቻችን ንቃት ከፍተኛ እንደሆነ፣ ያለው ችግር ሳይበግራቸው፣ ያለው ፈተና፣ ያለው መከራ ሳይበግራቸው፣ ያንን ዋጥ አድርገው፤ ትልቁን ምስል ነበር የሚያሳዩት። ሀገራዊ የሆነውን ነበር የሚያሳዩት” ሲሉ በዚህ ሁኔታ በግላቸው መደነቃቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አንስተዋል።
ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላለው አለመግባባት እና ግጭት ምክንት የሆኑ ጉዳዮችን በውይት መፍታት እንዲቻል ተልዕኮ በመያዝ ነበር ከሶስት ዓመት በፊት የተቋቋመው፡፡
ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልሎች ውጪ ባሉት ሁሉም ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ የትግራይ አጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል፡፡