ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ እጅግ ፈጣን ያለውን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ሁለተኛውን ጣቢያ በይፋ ሥራ አስጀምሬያለሁ ብሏል።
ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከቦሌ ወደ መገናኛ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ 16 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል የኤሌክትሪክ መኪና መሙያዎችን የያዘ ጣቢያ ገንብቼ ወደ ስራ አስገብቻለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም ከየካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ14 ሺህ 280 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት መስጠት ችሏል ተብሏል።
ለዚህም 376,574.72 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም ላይ ውሏል የተባለ ሲሆን በተጨማሪም 521,074.23 ኪሎግራም ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ መከላከል የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከ2,622 በላይ ዛፎችን ከመትከል ጋር እንደሚነጻጸር ተገልጿል።
በምራፍ ሁለት ወደስራ የገባው ሁለተኛው ጣቢያ በልዩ ሁኔታ የአውሮፓ ስሪት የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪኖችን (European EV Cars) ኃይል የመሙላት አቅም ያለውና ከተሽከርካሪዎቹ ጋር የተጣጣመ ኃይል መሙያ (EU Altra Fast) ቻርጀር ያለው እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል።
የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያው በአንድ ጊዜ እስከ 16 የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቻርጅ በማድረግ ለአሽከርካሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም ተብሏል።
በዚህም በአንድ ጊዜ በአጠቃላይ ለ32 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት መቻሉም ተገልጿል።
በተለይም አሽከርካሪዎች የቦታ ጥበት ሳያሳስባቸው ወደ ጣቢያው ገብተው አገልግሎታቸውን አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችል ሰፊና ምቹ ቦታ ላይ መገንባቱም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የኤሌክትሪክ መኪና ኃይል መሙያዎቹ እንደ መኪናው ሞዴል እና የባትሪ አቅም በሰከንድ 1 ኪ.ሜ የሚያስኬዳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ቻርጅ ማድረግ ይችላም ተብሏል።
ሲስተሙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የባትሪ መስፈርቶች እና የደንበኛን ትዕዝዝ ተቀብሎ በመመርመር በተፈለገው መጠን ቻርጅ ለማድረግ ያስችላል፡፡
አዲሱ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያው አራት እጅግ በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያዎች (እስከ 600 kW ድረስ ቻርጅ የማድረግ አቅም ያላቸው)፣ እንደ መኪናው አቅም በ15 ደቂቃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ (100%) የኤሌክትሪክ ኃይል መሙላት እንደሚያስችል ተገልጿል።
አገልግሎቱ በክፍያ ይሰጣል የተባለ ሲሆን የክፍያ ተመኑ በቴሌብር ሱፐር አፕ ላይ እንደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።