ኢትዮጵያ በአጼ ሀይለስላሴ አስተዳድር ዘመን የስቶክ ግብይት የሚፈቅድ ስርዓት የነበራት ቢሆንም በደርግ ዘመን ተቋርጦ ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ከ50 ዓመት በኋላ የስቶክ ግብይትን ዳግም ያስጀመረች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አስጀምረዋል፡፡

በዚህ የግብይት ስርዓት መሰረት ኩባንያዎች አክስዮኖቻቸውን በይፋ ለገዢዎች መሸጥ የጀመሩ ሲሆን ሸማቾች ደግሞ ለሚገዙት አክስዮን ዋስትና የሚሰጥ ተቋምም ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ይህን የአክስዮን ግብይት የሚያሳልጡ ሁለት መንግስታዊ ተቋማት የተቋቋሙ ሲሆን የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬት እና የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የስቶክ ግብይትን ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመር እቅድ የነበራት ቢሆንም ዘግይቶ ተጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር 39 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች የግል ኩባንያዎች በአዲሱ የስቶክ ማርኬት ለገዢዎች እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡
መንገስት በብቸኝነት የቆጣጠረውን ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ 10 በመቶ ድርሻ ለህዝብ ለመሸጥ ከሁለት ወር በፊት ይፋ ያደረገ ሲሆን የአክስዮን ሽያጩ በቴሌ ብር መተግበሪያ አማካኝነት ተካሂዷል፡፡
100 ቢሊየን ብር ጠቅላላ ሀብት ያለው ኢትዮ ቴሌኮም የ30 ቢሊዮን ብር አክስዮኑን ለሽያጭ አቅርቧል፡፡
አንዱን የድርጅቱን አክስዮን ዋጋ በ300 ብር እንደሚሸጥ ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም አንድ ግለሰብ መግዛት የሚችለው 33 አክስዮን ወይም 9 ሺህ 900 ብር ነውም ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮ ቴሌኮም 3 ሺህ 333 አክስዮኖቹን ለሽጭ ያቀረበ ሲሆን 30 ቢሊዮን ብር ከአክስዮን ሽያጭ ለማግኘት ማቀዱን በወቅቱ ተገልጾ የነበረ ሲሆን የመሸጫ ጊዜው ከአንድ ሳምንት በፊት ተጠናቋል፡፡