ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣም ነበር፡፡
የሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ቱርክ በአንካራ የውይይት መድረክ ያዘጋጀች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ በአንካራ መስማማታቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት ተናግረው ነበር፡፡
በቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አደራዳሪነት የተስማሙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት ለማክበር ኢትዮጵያም የወደብ አገልግሎት ከሶማሊያ እንደምታገኝ ተስማምተውም ነበር፡፡
ከአንካራው ስምምነት በኋላ የሶማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የደህንነት ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተወያይተዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴን የሶማሊያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሊ ጋር መወያየታቸውነ በትዊትር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ሬድዋን በጽሁፋቸው ላይ አክለውም የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ ለተግባራዊነቱ መስራት እንደሚባም ሁለቱም ወገኖች ትኩረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡
የአንካራውን ስምምነት ለማደናቀፍ የቅርብ እና የሩቅ አካላት አሉ ያሉት ሬድዋን ሁለቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጣልቃ ገብነትን ላለመፍቀድ ተስማምተዋልም ብለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብጽ አቻቸው ጋር መምከራቸው ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ግብጽ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሞቃዲሾ እንደምትልክ፣ ከቀይ ባህር ጋር የማይዋሰን ሀገር በአካባቢው መንቀሳቀስ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ሌላ መግለጫ ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጌዶ ግዛት ልዩ ቦታው ዶሎ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ሲል ከሷል። ጥቃቱ የሶማሊያን የጸጥታ ሀይሎች እና ንጹሀን ዜጎች ላይ ትኩረቱን አድርጓልም ተብሏል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሶማሊያ አቻው የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጓል፡፡ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያቀረበችው ክስ ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ በአንካራ የተስማሙትን ስምምነት እንዳይተገበር በሚፈልጉ አካላት ግፊት የተደረገ ነውም ተብሏል።