የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በሐረር ከተማ የታሸጉ 35 የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲደረግ ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቤቱታ አቅርቧል።
የክልሉ መንግስት ቅርንጫፎቹ የታሸጉት “ግንባታቸው ባላለቁ ህንጻዎች አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ ነው” ቢልም፤ ማህበሩ ግን ከሌሎች የንግድ ድርጅቶች በተለየ መልኩ እርምጃው በእነርሱ ላይ መወሰዱ ለክልሉ የኮሪደር ልማት የተጠየቀው መዋጮ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የተፈጸመ እንደሆነ “ከድምዳሜ ላይ እንዲደርስ” እንዳደረገው ገልጿል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
በሀረሪ ክልል የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ባንኮች የሁለት ሚሊዮን ብር “ድጋፍ” እንዲያደርጉ በደብዳቤ የተጠየቁት የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ነበር።
ደብዳቤውን ለባንክ ቅርንጫፎች የጻፈው የሀረሪ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ፤ የገንዘብ መጠኑን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ቀነ ገደብ ሰጥቷቸውም ነበር።
ሃያ ስድስት ባንኮችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር፤ ከትላንት በስቲያ ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጻፈው ደብዳቤ፤ የባንክ ቅርንጫፎች የተጠየቁትን ያህል የገንዘብ መጠን በመዋጮ መልክ ለመክፈል “ስልጣን እንደሌላቸው” ገልጿል።
የገንዘብ መዋጮ ጥያቄው በባንኮቹ “ዋና መስሪያ ቤት ታይቶ” እንዲሁም “በቂ በጀት የተመደበለት መሆኑ ተረጋግጦ” የሚፈቀድ መሆኑንም ማህበሩ አመልክቷል።
ክልሉ ያቀረበው ጥያቄ ለየባንኮቹ ዋና መስሪያ ቤት ተልኮ እየታየ ባለበት ወቅት፤ የሐረር ከተማ አስተዳደር 35 የባንክ ቅርንጫፎችን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንዲታሸጉ ማድረጉን ማህበሩ አስታውቋል።
እርምጃው የተወሰደባቸው ምክንያቶች በሚል ለባንክ ቅርንጫፎቹ በቃል ከተነገራቸው ውስጥ “ግንባታው ያላለቀ ህንጻ ውስጥ መስራት አትችሉም” የሚለው እንደሚገኝበት በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል።
ባንኮቹ ቅርንጫፎቹን የከፈቱባቸው ህንጻዎች “የግንባታ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው” የሚለው ሌላኛው በምክንያትነት የተነሳ ጉዳይ እንደሆነ ማህበሩ ገልጿል።
የህንጻዎቹ ባላቤቶች “የአከራይ እና ተከራይ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው” የሚሉትም እንዲሁ ለባንክ ቅርንጫፎቹ በቃል ከተነገራቸው ምክንያቶች ውስጥ እንደሚገኝበት የማህበሩ ደብዳቤ አትቷል።
እነዚህን ምክንያቶች መሰረት አድርጎ በባንክ ቅርንጫፎቹ ላይ የተወሰደው የእግድ እርምጃ “በተመሳሳይ ህንጻ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ ሌሎች ንግድ ድርጅቶችን ያልተመለከተ” መሆኑን ማህበሩ በማነጻጸሪያነት አንስቷል።
ከባንክ ውጪ ያሉ የንግድ ድርጅቶቹ በአሁኑ ወቅት ስራቸውን “ያለምንም እንከን እያከናወኑ ይገኛሉ” ያለው ማህበሩ፤ እርምጃው የባንክ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለይቶ ተግባራዊ መደረጉ “ለኮሪደር ልማቱ የተጠየቀው መዋጮ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የተፈጸመ እንደሆነ ከድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አድርጎናል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
የሀረሪ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኤል ዩሱፍ፤ በባንክ ቅርንጫፎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ከኮሪደር ልማት መዋጮ ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የባንክ ቅርንጫፎቹ “መዋቅሩ ተሰርቶ ያላለቀ” ህንጻ ላይ ባንኮች ተከራይተው እንደሚገቡ እና “ከላይ ግንባታ መሰራቱ ትክክል አለመሆኑን” ኃላፊው አስረድተዋል።
መስሪያ ቤታቸው ከሶስት ወራት በፊት ባላለቁ ህንጻዎች ላይ ያሉ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችን ጭምር ሲያሽግ እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል።
የህንጻዎቹ ባለቤቶች የግንባታ ማጠናቀቂያ ስራ “በአንዴ የሚያልቅ” ባለመሆኑ፤ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ምን ያህሉን የህንጻ ክፍል መገንባት እንደሚችሉ ለቢሮው በፈርማ መተማመኛ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።
ቢሮው ከወራት በኋላ ባደረገው ግምገማ፤ ቃል የተገባባቸው ስራዎች ባለመሰራታቸው ወደ ማሸግ እርምጃ መግባቱን አቶ ኢስማኤል አብራርተዋል።
የሀረሪ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማት እና ኢንዲስትሪ ቢሮ ኃላፊ በሐረር ከተማ አሁንም ያልታሸጉ ብዙ የባንክ ቅርንጫፎች እንዳሉ ቢገልጹም፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ግን የማሸግ እርምጃው “አሉታዊ ውጤት” “በሐረር ከተማ ብቻ ሳይወሰን ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተርፏል” ሲል በአቤቱታ ደብዳቤው ላይ አስፍሯል።
ባንኮች የፋይናንስ ተቋም ከመሆናቸው አንጻር “በደንበኞች እና የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል” ብሏል ማህበሩ።