ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣም ነበር፡፡
የሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ቱርክ በአንካራ የውይይት መድረክ ያዘጋጀች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ በትናንትናው ዕለት ወደ አንካራ አቅንተው ነበር፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች በተናጠል አግኝተው እንዳወያዩ አናዶሉ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ኢትዮጵያ እና ሱማልያ ሀለቱንም ሀገራት በሚያግባባ መልኩ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ኤርዶጋን ሁለቱ ሀገራት በጋራ ይፋ የሚያደርጉት የስምምነት ዶክመንት እንደተዘጋጀ ጠቅሰው ዶክመንቱ ሀገራቱ የበፊቱን ሳይሆን መጪውን ግዜ እንዴት በጋራ አብረው ተከባብረው እና በመልካም ጉርብትና እንደሚወጡት የሚያሳይ ነው ብለዋል፣ ለዚህም ሁለቱን ሀገራት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከህልውናዋ ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተው የዛሬው ውይይት ወደ ጓደኝነት መልሶናል ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማልያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ በበኩላቸው ዛሬ ምሽት የተደረገው ውይይት በቅርብ ግዜ በሀገራቸው እና ኢትዮጵያ መሀል የነበረውን አለመግባባት ያስቆመ ነው ብለዋል።
ሱማልያ የኢትዮጵያ “እውነተኛ ጓደኛ” ሆና ትቀጥላለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጦር በሶማልያ ለአመታት የከፈለውን መስዋዕትነትም ፕሬዝደንቱ አንስተዋል።
የአንካራው ስምምነት “በሶማልያ መንግስት ባለመብትነት ስር በሚከናወን የንግድ ውል፣ ሊዝ እና ሌላ አሰራር ሁለቱም ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ይከናወናል፣ ይህም ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር የመጠቀም እድል ይኖራታል። ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም ከመጋቢት 2017 ዓ/ም በፊት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሙ የማመቻቸት ስራ ይሰራል፣ በአራት ወር ውስጥ ደግሞ ስምምነት ይፈረማል።” እንደሚል ዘግይቶ የወጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡
ይሁንና የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ከአንድ ዓመት በፊት በአዲ አበባ ያደረገችው የወደብ ስምምነት እጣ ፈንታ እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ከሁለት ቀናት በፊት በርበራ ወደብ የኢትዮጵያ ትራንዚት ማሳለጫ ቢሮዎች ስራ ጀምሯል መባሉ ይታወሳል፡፡