አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የሮጠበት ማልያ በ2400 ዶላር ተሸጠ

በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስኬታማ አትሌት የሆነው ሀይሌ ገብረስላሴ የሮጠበት አንድ ማልያ በ2 ሺህ 400 ዶላር ተሸጧል፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደ በዚህ ጨረታ ላይ የቀረበው ይህ ማልያ አትሌት ሀይሌ በ1992 በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ በተካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ውድድርን ያሸነፈበት ማልያ ነበር፡፡

ይህ ውድድር ለአትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የጀመረበት ወቅት እንደነበርም ተገልጿል፡፡

የታላቁ ሩጫ መስራች እና ባለቤት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ለጨረታ ቀርቦ 2 ሺሕ 400 ዶላር የተሸጠው ማልያ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለማጠናከር ይውላልም ተብሏል፡፡

በጨረታው የታላቁ ሩጫ ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ የኃይሌ ገ/ሥላሴ የሮጠበት ማልያ፤ በእንግሊዛዊ ተጋባዥ እንግዳ አሸንፏል።

ይህንን የማልያ ጨረታ እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ሰው አሸነፈ ከመባሉ ውጪ ስለ አሸናፊው ማንነት አልተገለጸም፡፡

በዝግጅቱ ላይ የተገኘው ኃይሌ ገብረሥላሴ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ታዳጊዎችን ለማፍራት እየስራ ያለውን ሥራ በማድነቅ፤ በጨረታ የተሸጠው ማልያ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማነቃቃትና ለሚሰሩ ማዘውተርያ ስፍራዎች እንደሚውል ገልጿል።

ኃይሌ በሩጫው መስክ የአገሩን ገጽታ በታላላቅ የዓለም መድረኮች ላይ ከማስተዋወቁ ባሻገር በተለያዩ የኢንቨሰትመንት መስኮች ውጤታማ መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት መልካሙ ተገኝ፤ ፌዴሬሽኑን ለማጠናከር ላደረገው ጠቃሚ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

ፌዴሬሽኑ አትሌቲክሱን ለማሳደግ ከሞሓ ለስላሳ  መጠጦች፣ ከጆርካ ኢቨንትና ከጎፈሬ የትጥቅ አምራች ጋር ስፖንሰር ሽፕ ስምምነት መፈራረሙን ያስታወሱት አትሌት መልካሙ፤ ውጤታማ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ለማካሄድ እና የማዘውተሪያ ስፍራ ለማስፋፋት የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም በስፖርት ታሪክ በማስታወሻነት የተቀመጡ ማልያዎች፣ ሜዳልያዎች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለጨረታ በማዋል ስፓርቱን ለማጠናከር በጋራ እንዲሰሩ ፌዴሬሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ባሳለፍነው እሁድ ሕዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ላይ 50 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በወንዶች በተካሄደው ውድድር የአምናው የውድድሩ አሸናፊ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ቢንያም መሐሪ 1ኛ በመውጣት ያሸነፈ ሲሆን፤ ውድድሩን በተከታታይ በማሸነፍም አዲስ ታሪክ ጽፏል።

በውድድረ አትሌት አዲሱ ነጋሽ 2ኛ ደረጃን በማያዝ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ፤ አትሌት ይስማው ድሉ ደግሞ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች በተካሄደው ውድድር አትሌት አሳየች አይቼው በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ የኔዋ ንብረት ሁለተኛ እንዲሁም ቦሰና ሙላቴ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ለ24ኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *