የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ እንዳሉት በቋሚ ደመወዝ ለሚተዳደሩ ሰራተኞች የሥራ ግብር መቀነስን ጨምሮ ሌሎች የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ እንደገለጹት ከብር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር ተያይዞ ቋሚ ደመወዝ የሚያገኙ ሰራተኞች ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
“በተለይም ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘው ሰራተኛ ቀን ቀን እየሠራ ማታ ማታ ሆቴሎች ላይ ፍርፋሪ እየለመነ እያደረ ነው።” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኑሮ ጫናው በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥረው በሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም ከዚህ በፊት በሰራተኞች የኑሮ ሁኔታ ዙርያ ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው ነገር ግን እነዚህ ውይይቶች ውጤት አለማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም የሥራ ግብር መቀነስን ጨምሮ ሌሎች የኑሮ ውድነት ጫናዎችን ሊያቀሉ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠቅላይ ሚንስትሩን በድጋሚ በደብዳቤ መጠየቃቸውን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡
መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ከሁለት ወር በፊት ይፋ ማድረጉ ታወሳል፡፡
በዚህ የደመወዝ ጭማሪ 2.3 ሚሊየን የፌደራልና የክልል መንግስታት የመንግስት ሰራተኞች፣ 56 ሺህ ተሿሚዎች፣ ለሀገር ደህንነት ሲባል ቁጥራቸው የማይቀመጠው የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የደሞዝ ማሻሻያው ተጠቃሚ ናቸው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለዝርዝር የደሞዝ መግለጫው በፃፉት መግቢያ “በተለይም ዝቅተኛ የደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱ እና ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም እንዲችሉ” የሚል አገላለፅ ተጠቅመዋል፡፡
በጭማሪው ዝቅተኛው የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ 4,760 ብር ሲሆን ቀድሞ ከነበረው 1,100ብር በመቶኛ የ332.7% ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡
ከፍተኛው የመንግስት ሰራተኛ ወርሃዊ ደመወዝ 20,468 ብር በ5% ጭማሪ 21,491ብር ደርሷል፡፡
የተጠበቀው ጭማሪ ቢደረግም ከ6,000 ብር በታች የሚያገኙት የመንግስት ሰራተኞች ድርሻ 47.9% በመቶ ሲሆን አሁንም አብዛኞቹ የመንግስት ሰራተኞች በወር ስድስት ሺህ ብር አልያም 55 ዶላር ብቻ የሚያገኙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር የመግዛት አቅሙ ከ100 ፐርሰንት በላይ የተዳከመ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ120 ብር እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እየጨመረ ሲሆን የመንግስት ሰራተኞች የበለጠ ተጎጂ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወስን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡