የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ሆን ብላ ጎርፍ እንዲፈጠር ውሃ እየለቀቀች ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ጎርፍ እንዲከሰት ሆን ብላ ከግድቦቿ ውሃ እየለቀቀች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዘኢኮኖሚስት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በሶማሊያ በጎርፍ የተጥለቀለቁ አካባቢዎችን ፎቶግራፎች አቅርበው፤ አደጋው ኢትዮጵያ ሆን ብላ ያደረገችው ነው ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ኢትዮጵያ በድንበር አቅራቢያ “በጎሳ ለተመሰረቱ ለሶማሊያ ሚሊሻዎች ትጥቅ እያስተላለፈች ነው” ሲሉም ተጨማሪ ክስ አቅርበዋል።
እነዚህ መሳሪያዎች በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው “በአልሸባብ እጅ ሊወድቁ ይችላሉ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ “የግብፅ ወታደሮች ስምሪትን እንዲቃወሙ በሶማሊያ ውስጥ ያሉ የጎሳ መሪዎችን እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን እያበረታታች ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ካደረገች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ሻክሯል፡፡
ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ የወሰደችው ሲሆን ተቋማቱ ሁለቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊያ ከግብጽ እና ቱርክ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ለማድረግ ስምምነት ያደረገች ኢትዮጵያ በበኩሏ ሞቃዲሾ ከግብጽ ጋር ያደረገችው ስምምነት እንደሚያሳስባት አስጠንቅቃለች፡፡
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞዓሊም ፊኪ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ከተገበረች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ታጣቂዎች ልንደግፍ እንችላለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ስምምነቱ ከተተገበረ ታጣቂዎችን አልያም የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል የሚታገሉ አማጺያን ጋር ለመገናኘት እንሞክራለን” ብለዋል፡፡
እስካሁን ታጣቂዎቹን ለማግኘት እየሞከርን አይደለም፣ ለችግሩ ሁሉ መፍትሄ ሊኖር እንደሚችል ተስፋ አለን” የሚሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ወደ መተግበር ከገባች ግን አማጺያኑን መርዳት የምችልበት መንገድ ይኖራል ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በታሪክ ሁለት ጊዜ ይፋዊ ጦርነት ያደረጉ ሲሆን በ1980ዎቹ እና 70ዎቹ ላይ አንዳቸው የሌላኛውን አማጺ ይረዱም ነበር ተብሏል፡፡
የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡