በኢትዮጵያ የሚገኙት በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በሀገሪቱ እያጋጠመን ይገኛል ባሉት ተግዳሮቶች ወደ ጎረቤት ሀገራት እየሄዱ መሆኑን ገለፁ
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ ቀዳሚ የሆኑት የቻይና ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ ሌሎች ሀገራት እየተሰደዱ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የቻይና ባለሃብቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠማቸው በመንግስት አመቺ የስራ ሁኔታዎች እየተሰጠ ባለመሆኑ ወደ ጎሮቤት ሃገራት ማለትም ወደ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ታንዛኒያ እያማተሩ እንደሚገኙ ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ተወካይ እንደተናገሩት በብዙ ምክንያቶች ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ንግዳቸውን ወደ ጎሮቤት አገሮች አዙረዋል ።
“ይህ ለኤምባሲው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ ስጋት ነዉ ምክንያቱም የእኛ ተልዕኮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ትብብር ማመቻቸት እንደመሆኑ ይህ ደግሞ በተለይ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትልቅ ስጋት ነዉ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ተወካይ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንዳለባት አረጋግጠዋል።
የመጀመሪያው የደህንነት ቀውስ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና እንዲሁም ግብይት ስርዓት እየጠበበ መምጣቱ ዋነኛው ምክንያቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ከግብር ጋር በተያያዘ ደግሞ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸው ሌላኛዉ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሁል ጊዜ “ከጉምሩክ ቢሮ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ቀረጥ” ከባድ አድርጎታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እንዳስታወቀው ቻይናውያን ባለሃብቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ኩባንያዎች በመክፈት ለራሳቸው ገንዘብ እያፈሩ ለኢትዮጵያ ዘመናዊነት ደግሞ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
እ.ኤ.አ. በግንቦት 2024 የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ከ2,000 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኢንቨስትመንት እና ከ600 ሺህ በላይ የሚጠጉ የስራ እድሎችን መፍጠራቸው የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይህ በዚህ እንዳለ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በቻይናዊን ኩባያዎች ምክንያት ከገበያ እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር የውጪ የግንባታ ስራ ተቋራጮች ከ 2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ለሚያወጡ ስራዎች ብቻ እንዲጫረቱ መንግስትን ጠይቀዋል፡፡
የውጪ ሃገራት ስራ ተቋራጮች በስፋት በኢትዮጵያ ውስጥ በመሰማራታቸው የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከገበያ ውጪ እየሆኑ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ሀብተማርያም ተናግረዋል::
ሕጉ የውጪ ተቋራጮች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ለሆነ ስራ ብቻ መጫረት አለባቸው ቢልም ይህ ተግባራዊ እየሆነ እንዳልሆነና ከ50 ሚሊዮን ብር ያነሰ ስራ ላይ ሳይቀር የውጭ ኩባንያዎች በተለይም ቻይናዊን እየተጫረቱ እንደሚገኙ ሰምተናል::
የውጪ ተቋራጮች በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በስፋት ቅድሚያ የሚያገኙበት አስራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቱ አፅእኖት የሰጡት::
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአዲስ መልክ እየተሻሻለ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም::