የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቦ ነበር
የገንዘብ ሚኒስቴር ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ 91.4 ቢሊየን ብር በጀት ይፋ ተደርጓል፡፡
መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ከአንድ ወር በፊት ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ የደመወዝ ጭማሪ 2.3 ሚሊየን የፌደራልና የክልል መንግስታት የመንግስት ሰራተኞች፣ 56 ሺህ ተሿሚዎች፣ ለሀገር ደህንነት ሲባል ቁጥራቸው የማይቀመጠው የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የደሞዝ ማሻሻያው ተጠቃሚ ናቸው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለዝርዝር የደሞዝ መግለጫው በፃፉት መግቢያ “በተለይም ዝቅተኛ የደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱ እና ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም እንዲችሉ” የሚል አገላለፅ ተጠቅመዋል፡፡
በጭማሪው ዝቅተኛው የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ 4,760 ብር ሲሆን ቀድሞ ከነበረው 1,100ብር በመቶኛ የ332.7% ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡
ከፍተኛው የመንግስት ሰራተኛ ወርሃዊ ደመወዝ 20,468 ብር በ5% ጭማሪ 21,491ብር ደርሷል፡፡
የተጠበቀው ጭማሪ ቢደረግም ከ6,000 ብር በታች የሚያገኙት የመንግስት ሰራተኞች ድርሻ 47.9% በመቶ ሲሆን አሁንም አብዛኞቹ የመንግስት ሰራተኞች በወር ስድስት ሺህ ብር አልያም 55 ዶላር ብቻ የሚያገኙ ናቸው፡፡
ቀሪ 41% የሚሆኑት የመንግስት ሰራተኞች ወርሃዊ ደመወዛቸው ከ6,000-10,600 ብር ሲሆኑ መደበኛ ድህነት ውስጥ ሲገኙ ገቢያቸው ከ10,556ብር በላይ የሚገኙትም ልዝብ ድህነት ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡
ይህ ልኬት በአለም አቀፍ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ወጪዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት የቤተሰብ ጥናት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ለመተመን የሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ምርታማነት፣ የሰራተኛው ወርሃዊ ፍጆታ እንዲሁም አንድ ሰው የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ ካሎሪ (የተመጣጠነ ምግብ ትመና) ማስላት ስለሚያስፈልግ መረጃዎቹ እስከሚጠቃለሉ ለዝቅተኛ ደሞዝ ትመና የሚጠጋጋ ማሻሻያ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የደመወዝ ማሻሻያ ያደረገችው ከስድስት አመታት በፊት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር የመግዛት አቅሙ ከ100 ፐርሰንት በላይ የተዳከመ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108 ብር እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እየጨመረ ሲሆን የመንግስት ሰራተኞች የበለጠ ተጎጂ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወስን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ለሰራተኞች የስራ ግብር እንዲቀነስ ፤ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም በድጋሚ ለመንግስት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“አሁንም በቀን_አንድ_ጊዜ ብቻ በልቶ ለመዋል የሚቸገር ሰራተኛ ነው ያለው” ያሉት አቶ ካሳሁን ሰራተኛው ካለው ገቢ አንፃር ችግሩ የሰፋ እንደሆነ አስረድተዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ አሁን ላይ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡