ለ17 ቀናት በፓሪስ የተካሄደው 33ኛው ኦሎምፒክ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ድል ያስመዘገቡ እና የተሳተፉ የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ዛሬ ማለዳ ነሀሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል።
የልኡካን ቡድኑ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በዛሬው እለት ከሰዓት በኋላ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ለልዑካን ቡድኑ የክብር ሽልማት፣ የማበረታቻ እና የእራት ግብዣ መርኃ-ግብር የሚካሄድ መሆኑንም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ 1 የወርቅ እና 3 የብር በአጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም 47ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 4ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።
ታምራት ቶላ በማራቶን ወርቅ፣ ጽጌ ድጉማ በሴቶች 800 ሜትር ብር፣ በሪሁ አረጋዊ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ብር እንዲሁም ትግስት አሰፋ በሴቶች ማራቶን ብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡
ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው የወንዶች ማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ ርቀቱን በ2:06:26 በሆነ ሰዓት አሸንፏል፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ ውድድሩን የጨረሰበት ሰዓት አዲስ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ እንዳሸነፈም ተገልጿል፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ በውድድሩ በ2:06:26 በሆነ ሰዓት በመግባት በወንዶች ማራቶን የኦሎምፒክ ሪከርድ ባለቤት መሆን ችሏል።
የ2024 ኦሎምፒክ አፍሪካውያን አትሌቶች ባልተጠበቁ ውድድሮች አሸንፈዋል።
ቦትስዋና በወንዶች የ200 ሜትር ሩጫ በሌስል ቶቦጎ አማካኝነት በኦሎምፒክ መድረክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በፓሪስ ማሳካት ችላለች።
አልጀሪያም በአርትስቲክ ጂምናስቲክ ለሀገሪቱ ብሎም ለአፍሪካ ቀዳሚውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ በካይሊያ ኔሞር አማካኝነት አሳክታለች።
የደቡብ ሱዳን የወንዶች የቅርጫት ኳስ ቡድን በፓሪስ ኦሎምፒክ በመክፈቻው ፖርቶ ሪኮን 90 ለ78 በማሸነፍ ያሳየው ብቃትም አፍሪካውያን ከተለመዱት የአትሌቲክስ ውድድሮች ውጪም ብሩህ ተስፋ እንዳላቸው ማመላከቱ ይታወሳል።
ከ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት በ33ኛው ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት የቻሉት 12ቱ ብቻ ናቸው።
አራት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አምስት የነሃስ ሜዳልያዎችን ያገኘችው ኬንያ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ደግሞ 17ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን በ1956 በሜልቦርን የጀመረችው ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከአፍሪካ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካን ተከትላ 4ኛ፤ ከአለም ደግሞ 47ኛ ደረጃን ይዛለች።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በኦሎምፒክ መድረክ ያገኘችውን የሜዳልያ ብዛት 62 አድርሳለች።
ከ206 ሀገራት ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት የፓሪስ ኦሎምፒክ በአሜሪካ የበላይነት ተጠናቋል።
40 የወርቅ፣ 44 የብር እና 42 የነሃስ ሜዳልያዎችን ያገኘችው አሜሪካ ከቻይና ጋር በወርቅ ሜዳልያ እኩል ብትሆንም በብርና ሜዳልያዎች ብዛት በመብለጥ የፓሪስ ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዥን በበላይነት አጠናቃለች።
አሜሪካ ካለፉት ሰባት ኦሎምፒኮች ስድስቱን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችላለች።
በአቴንስ በፈረንጆቹ በ1896 ከተደረገው ኦሎምፒክ አንስቶ በተደረጉ የኦሎምፒክ ውድድሮች በ19ኙ አንደኛ ሆና በማጠናቀቅም ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች።
የዘንድሮው ኦሎምፒያድ አዘጋጅ ፈረንሳይ ደግሞ ጃፓን እና አውስትራሊያን ተከትላ አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
32 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች በተካሄዱበት የፓሪስ ኦሎምፒክ 91 ሀገራት በሜዳልያ ሰንጠረዡ ውስጥ ገብተዋል።