የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል ባለሃብቶችንና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ይጎዳል በማለት ተቃውሟል፡፡
ኮሚሽኑ ለትራንስፖርት ሚንስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የሕግ ድንጋጌ ሳይኖርና ግልጽ ሕግ ሳይወጣለት ከበላይ አካል በተሰጠ ትዕዛዝ ብቻ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ማገድ አግባብነት የለውም በማለት ቅሬታውን እንደገለጠ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተላለፈው ውሳኔ በግብርና፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በአበባ እርሻ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግና ግንባታ እና ሌሎች ስራዎች በተሠማሩ ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ አክሎም ለአንዳንድ ኢንቨስትመንት ስራዎች ከባሕሪያቸው አንጻር በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዲያስገቡ እንዲፈቀድላቸው ሲል እንደጠየቀም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ካሳለፍነው መጋቢት ወር ጀምሮ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ ለሙሉ ማገዷ ይታወሳል፡፡
መኪኖችን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ስራ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንዳሉት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እንደማይችሉ በመንግስት ታግደዋል።
ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከአውሮፓና ደቡብ አፍሪቃ ያጓጓዟቸውን በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ማስገባት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል። በመኪና ማስመጣት ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ሰዎችም በእገዳው ሳቢያ ከፍተኛ መጉላላትና ኪሳራ እንደደረሰባቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ከአራት ወር በፊት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማገዱን ለፓርላማ አባላት ሲያስታውቅ የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ እገዳው ተገባራዊ እንደማይደረግና በዕቅድ ደረጃ ያለ መሆኑን ተናግሮ ነበር።
ይሁንና ከመጋቢት ጀምሮ የተለየ ፍላጎት ላላቸው የልማት ፕሮጀክቶችና ለህዝብ ትራንስፖርት የሚውሉ ካልሆኑ በቀር በነዳጅ የሚሰሩ የግል ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ታግደዋል።
መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ የግል ተሽከርካሪዎችን ያገደው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የነዳጅ ወጪውን ለመቀነስ መሆኑን ገልጿል።
መንግስት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የባትሪ መኪኖችን እንደሚያበረታታና እንደሚያስፋፋም ሚንስትሩ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተሸከርካሪ እንዳለ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳይ ሲሆን አብዛኞቹ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው፡፡
ከአረጁ ተሸከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ለመከላከል ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ አገልግሎት የሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ተጥሎባቸዋል፡፡
እንዲሁም አዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ መኪና አስመጪዎች ደግሞ ዝቅተኛ ግብር እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ ሲሆን በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ አዲስ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የበለጠ የግብር እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ያገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዢ ማውጣት እንደማትችል ገልጸው ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስመጡ እና በሀገር ውስጥ መገጣጠም እንዲጀምሩ መንግስትም ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡