ዋና መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው ሳፋሪኮም ኬንያ የደንበኞቹን መረጃ ለመንግስት እንዳልሰጠ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የአገሪቱን የመረጃ ጥበቃ ህግ መሰረት በማድረግ የደንበኞቹን ነፃነት እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡
ተቋሙ እንዳለው በፍርድ ቤት አማካኝነት ካልታዘዘ በስተቀር ማንኛውንም የደንበኞቹን መረጃ ለሌላ ሶስተኛ አካል አሳልፎ እንደማይሰጥ ገልጿል፡፡
ድርጅቱ እስካሁን የደንበኞቹን መረጃ እንዲሰጥ ከመንግስት ጥያቄ እንዳልቀረበለት አስታውቋል፡፡
እንዲሁም የደንበኞቹን መረጃ ለመንግስት አካል አሳልፎ እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዳልደረሰውም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
የድርጅቱ እህት ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ በሚል ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ህጋዊ ፍቃድ ከተቀበለ ከአንድ ዓመት በኋላ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሳፋሪኮም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕን ያካተተ ነው።
ኢትዮጵያ ለውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በሯን መክፈቷን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት ነሀሴ 2014 ዓ.ም ላይ በድሬዳዋ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለ50 በመቶ ህዝብ እንዲሁም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 98 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የቴሌኮም አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለአል ዐይን እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለኔትወርክ ማስፋፊያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድቤያለሁ ብሏል፡፡
ተቋሙ አክሎም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችበተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 5 ሺህ አዳዲስ የኔትወርክ ማማዎችን እንደሚተክልም አስታውቋል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት የኔትወርክ አገልግሎቱን ለደንበኞቹ እየሰጠ መሆኑን ያሳወቀው ሳፋሪ ኮም ቀስ በቀስ የራሱን የኔትወርክ መስመሮች እየገነባ እንደሆነም ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ድርጅቱ በ2 ሺህ 500 የኔትወርክ ማማዎች አገልግሎት እየሰጠሁ ነው የሚለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 500 ያህሉ ራሴ የገነባኋቸው ናቸውም ብሏል፡፡