የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለቀጣዮቹ 3 ዓመታት የዓለም ሥራ ድርጅት አስተዳድር አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡
በጀኔቫ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ባለው የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) 112ኛ ጉባኤ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው ስብሰባ ለቀጣይ 3 ዓመታት በበላይነት የሚቆጣጠሩና የሚያስተዳድሩ አካላትን ከሠራተኞች ፣ከመንግሥታትና ከአሠሪዎች መካከል ለመምረጥ ባደረገው እንቅስቃሴ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ባገኙት ከፍተኛ ድምፅ የዓለም ሥራ ድርጅት የሚያስተዳድረው አካል አባል በመሆን መመረጣቸው ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ 112ኛ ጉባኤ ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2016 ባካሄደው ስብሰባው የዓለም ሥራ ድርጅትን በበላይነት የሚያስተዳድር (Governing Body) ምክትል አባል ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን አንዷ አድርጎ መርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከተወዳደሩት ሰባት ሀገራት መካከል ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነው የተመረጠችው።
ከተለያዩ አባል ሀገራት የተውጣጡ የመንግሥት 28 አባላት ተወካዮች፣ አሠሪን የሚወክሉ 14 አባላት እና ሠራተኞችን የሚወክሉ 14 አባላት ያሉት የሚያስተዳድረው ይህ የበላይ አካል አባላት በየሶስት አመቱ በዓለም አቀፍ የሥራ ጉባኤ ይመረጣሉ፡፡
ከመንግሥት መቀመጫዎች ውስጥ አስሩ ዋና ዋና የኢንዱስትሪ ጠቀሜታ ባላቸው ሀገራት በቋሚነት የተያዙ ሲሆን የተቀሩት የመንግሥት መቀመጫዎች በመንግሥታት ተወካዮች ይመረጣሉ ።
ድርጅቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው አባል ሀገራት የዓለም ሥራ ድርጅት (የILO) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አካል ሲሆን የድርጅቱን ዋና ዳይሬክተር ምርጫን ጨምሮ በድርጅቱ ፖሊሲዎች፤ ፕሮግራሞችንና በጀት ላይ ለሚቀጥሉት 3 አመታት የሚወስን አካል ነው፡፡
ምርጫዎቹ ጉባኤው የአባል ሀገራቶች የመንግሥታት፣ የአሠሪና የሠራተኞች ተወካዮችን ያሳተፉ ሲሆን ቀደም ብለው በወጡ እና መጨመር ባለባቸው የዓለም ሥራ ድርጅት ድንጋጌዎች ላይ የሶስቱም አካላት፣ በተናጠልና በጋራ እየመከሩ ይገኛል።
ይህም ሀገራችን በድርጅቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የድርጅቱን ሥራ በቅርብ ለመከታተልና ከድርጅቱ ተገቢውን ድጋፍ ለማግኘት ካለው ፋይዳ ባለፈ የአገራችንን ተደማጭነት በመጨመር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውክልና ከፍ በማድረግ የገፅታ ግንባታችንን እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ደረጃችንን ያሳድጋል የሚል እምነትን አሳድሯል።
በሠራተኞች ተወካዮችና በመንግስታቶች መካከል በተደረገው የሚያስተዳድሩ አካል ምርጫ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በከፍተኛ ድምፅ አባል ለመሆን ማሸነፋቸው ኢትዮጵያ የዓለም ሥራ ድርጅትን ከሌሎች ጋር በመሆን እንድትሰራ ይስችላታል ተብሏል፡፡
የዓለም ስራ ድርጅት አስተዳድር አካል የዓለም ሥራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ከመሾም ጀምሮ፣ የዓለም ሥራ ድርጅት ስምምነቶችን እና በአባል ሀገራት የተሰጡ ምክሮችን አፈፃፀም የሚገመግምና የዓለም አቀፍ የሥራ ደረጃዎችን መጣስ በተመለከተ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የሚመለከት ወሳኝ አካል ነው፡፡
የዓለም ሥራ ድርጅት የበላይ አካል ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፋፋት እና በአለም አቀፍ የሥራ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ድርጅቱ የሚያደርገውን ጥረት በመምራት ረገድ ወሳኝ ሚናም ይጫወታል።