ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለው ሰላም አስከባሪ ጦሯን ልታስወጣ ነው

በሶማሊያ የሰፈረው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በቀጣይ ታህሳስ ወር ሀገሪቱን ለቆ ይወጣል ብሎ እንደሚጠብቅ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሶማሊ ከላኩ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ ጦራቸውን ወደ ሶማሊያ የላኩ ሀገራት ናቸው፡፡

ሶማሊያ በሀገሯ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ የሚገኙ ሁሉም የኢትዮጵያ ወታደሮች በመጪው ታህሳስ ወር ላይ ሙሉ ለሙሉ ጠቅልለው ይወጣሉ ብላ እንደምትጠብቅ አስታውቃለች።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሼክ አሊ ለቪኦኤ እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (ATMIS) በቀጣይ አመት ታህሳስ ወር ተልዕኮው ካበቃ በኋላ “የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሃይል አባል አይሆኑም” ብሏል።

የፕሬዚዳንቱ የደህንነት አማካሪው አክለውም ከቀጣይ አመት በኋላ በሶማሊያ በሚሰፍረው ጦር ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደማይኖሩ እና ከሌሎቹ የሰላም አስከባሪ ሀይል ካበረከቱ አራቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ የተውጣጡ ብቻ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በሶማሊያ ሰላም በማስከበር ላይ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በመጪው ታህሳስ ወር ላይ በሶማሊያ የሰፈረው የሰላም አስከባሪ ጦር ሀገሪቱን ለቆ ይወጣል።

ይሁን እንጂ የሰላም አስከባሪው ሀይሉ ለቆ ከወጣ በኋላ ዋና ዋና የህዝብ ማዕከላትን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እና የሀሪቱ መንግስት ቁልፍ ተቋማትን በመቆጣጠር ጸጥታ የሚያስከብር ሀይል ለማቋቋም እዕቅ መኖሩ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአምስት ወራት በፊት በወደብ ጉዳይ በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን ሶማሊላንድ ደግሞ የሀገርነት እውቅና እንድታገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና እና ተቃውሞን አስከትሏል።

ከአንድ ወር በፊት ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደርን በ72 ሰዓት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ እና በሀርጌሳ እና ጋሮዌ ያሉ የቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ሰራተኞቹም በሁለት ሳምንት ውስጥ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኗን አስታውቃ ነበር፡፡

በወቅቱም ራስ ገዟ ሶማላንድ እና ፑንት ላንድ የሶማሊያ መንግስት በሀርጌሳ እና ጋሮዌ የሚገኙ ቆንስላዎች እንዲዘጉ ያሳለፈውን ውሳኔ መቃወማቸው አይዘነጋም።

ከሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት በኋላ ሶማሊያ የባህር በሯን በቱርክ ለማስጠበቅ በሚል ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረትም ቱርክ የሶማሊን ባህር ትጠብቃለች፡፡

ኢትዮጵያ የሶማሊያ እና ቱርክ ስምምነት ዙሪያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ለመፈጸም እንቅፋት አይፈጥርም በሚል ለቀረበው ጥያቄ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አያሳስበኝም ብላለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *