ኢትዮጵያ ባለፋት አስር ወራት ከአበባ ኤክስፓርት ከ 3 መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች፡፡
የሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለይም የአበባ ኤክስፖርት ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦን እያበረከተ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ አበበ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ባለፋት አስር ወራት 79 ሺህ 819 ቶን የአበባ ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 392 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በአብዛኛው ወደ አውሮፓና ኤዥያ ሀገራት እንደሚላክ የተናገሩት ስራ አስፈፃሚው ምርጥ አስር ተብለው ከተለዩት ተቀባይ ሀገራት መካከል ደግሞ ኔዘርላንድ ትልቁን ድርሻ ትይዛለች ብለዋል።
በበጀት አመቱ አስር ወራት ከእቅድ አፈፃፀም አንጻር ሲታይ የተገኘው ገቢ ጥሩ ነው ቢባልም ኢትዮጵያ በዘርፏ ካላት አቅም እና ጥሩ የሆነ ስነምህዳር አኳያ ሲታይ ግን በቂ አለመሆኑ ተጠቅሷል።
ምንም እንኳን ዘርፏ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ገቢን በማስገኘት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ቢባልም የሆርቲካልቸር የወጪ ንግድ ውስጣዊና ውጫዊ በሆነ አለም አቀፍዊ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ ይገኛል ሲሉ አቶ ደረጀ ገልፀዋል፡፡
ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና የመሬት ማስፋፊያ ጥያቄዎችን በአግባቡ ካለማስተናገድ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከዘርፉ በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳልተገኘ ተናግረዋል፡፡
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከምንግዜውም በላይ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም ለችግሮቹ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል ተብሏል።
ብሪታንያ ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ሀገራት አበባ ያለ ግብር ወደ ሀገሯ እንዲገባ መፍቀዷ ይታወሳል፡፡
የብሪታንያ ንግድ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ብሪታንያ የአበባ ምርቶችን ወደ ሀገራቸው በሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጥላው የነበረውን ግብር አንስታለች፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ በፊት የአበባ ምርቶች ወደ ብሪታንያ ሲገቡ 8 በመቶ ግብር መክፈል የነበረባቸው ሲሆን ከዛሬ ሚያዚያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ማንሰቷን አስታውቃለች፡፡
የብሪታንያ ንግድ ኮሚሽነር ጆን ሀምፍሬይ እንዳሉት ወደ ብሪታንያ የሚገቡ የአበባ ምርቶች ከግብር ነጻ መሆናቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አበባ አምራች እና ነጋዴዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ በብሪታንያ የአበባ ምርት በቅ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል አበባ ላኪ ሀገራት ናቸው፡፡
እነዚህ አምስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀጥታም ይሁን በሶተኛ ሀገር አድርገው ወደ ብሪታንያ ለሚያስገቡት የአበባ ምርት የገቢ ግብር አይከፍሉም ተብሏል፡፡
ብሪታንያ ወደ ሀገሯ ለሚገቡ የአበባ ምርቶች ይፋ ያደረገችው የግብር እፎይታ ለሁለት ዓመት እንደሚቆይ አስታውቃለች፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ካላት ፍላጎት የተነሳ መሆኑንም አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ በ2023 ዓመት ብቻ 12 ነትብ 6 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ያላቸው የአበባ ምርቶችን ወደ ብሪታንያ መላኳ ተገልጿል፡፡
ከአፍሪካ ሁለተኛ የአበባ አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከሚመረተው ጠቅላላ የአበባ ምርት ውስጥ 23 በመቶውን ትሸፍናለች፡፡
ኬንያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አበባ አምራች ሀገር ስትሆን በዓለም ላይ ከሚመረተው ውስጥ የ6 በመቶ ድርሻ በመያዝ አራተኛዋ አበባ አምራች ሀገር እንደሆነች ተገልጿል፡፡