የኢትዮጵያ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ወይም ስታርት አፕ የተለያዩ ማበረታቻዎችን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ለስራ ፈጣሪዎች ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ከግብር ነጻ እድል፣ ከውጭ ንግዶች የሚያገኟቸውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ሙሉ ለሙሉ እንዲወስዱ፣ ንግድ ፈቃድ ለማውጣት የግድ ቢሮ ያስፈልግ የነበረውን ማንሳት፣ አዲ ሀሳብ ላላቸው ብድር ማመቻቸት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ይህ አውደ ርዕይ ለ20 ቀናት ይቆያል የተባለ ሲሆን ጎብኚዎች ወደ ሳይንስ ሙዚየም በማቅናት መግባት እና መጎብኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል በሚፈልጉበት ወቅት ያለምንም የንግድ ቤት ኪራይ ውል ሥራ መጀመር የሚችሉበትን አዲስ አሠራር መዘርጋቱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ሀገር ፈንድ ያገኘ ስታርት አፕ ሙሉ በሙሉ የውጭ ምንዛሪውን ለሚፈልገው ሥራ ማዋል የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
አዲስ ፈጠራ ያላቸውና ሥራቸው ወደ ገቢ መቀየር የሚችሉ ወጣቶች በውጭ ሀገራት ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ በሚጠየቁበት ወቅት በባንኮች በኩል መንግሥት በሚያመቻቸው አሠራር ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት አማራጭ እንደሚመቻችላቸው ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በፈጠራ ላይ ለተመረኮዙ ቴክኖሎጂ መር ሥራ ፈጣሪዎች በጉምሩክ አሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ክፍያዎችን የሚቀንስና፣ የጉምሩክ ድጋፍ የሚያገኙበት ማዕከል እንደሚቋቋምም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የስታርት አፕ ዓውድ በማስፋት ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሱበትን ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራዎችን ማሳደግ እንደሚያስፈልም ጠቁመዋል።
ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ሲባልም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ህጎች ዳግም እንደሚሻሻሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት በሚልም የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን እንደሚከተልም ተገልጿል፡፡
የልማት ባንክ የተሻለ እና አዲስ የስራ እና ቢዝነስ ሀሳብ ይዘው ለሚመጡ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ብሔራዊ ባንክም የኢትዮጵያ ባንኮች ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ምቹ አሰራር መዘርጋት እንዲችሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ስራ አጥ እንደሆኑ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሪፖርት የሚያስረዳ ሲሆን በየዓመቱ 2 ሚሊዮን የስራ እድል ካልተፈጠረ የኢኮኖሚ እና መህበራዊ ቀውስ ስጋት ይደቅናል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ 200 ሺህ ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመጀመሪያ ድግሪ እና ከዛ በላይ እንደሚመረቁ የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያስረዳል፡፡