ኢትዮጵያ በሳውዲ አረቢያ ያሉ 70 ሺህ ዜጎቿን ወደ ሀገራቸው ልትመልስ ነው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮያውያንን ወደ ሀገራቸው እመልሳለሁ ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ “በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው የመመለስ ሦስተኛ ምዕራፍ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይጀምራል” ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮያውያንን ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ መክሯል።

የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ በብሔራዊ ኮሚቴው ውስጥ የታቀፉት የፌዴራል ተቋማት እና የክልሎችን የጋራ ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።

ከወዲሁ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተሟላ ሁኔታ በፍጥነት መጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል።

አምባሳደር ብርቱካን ዜጎችን የማስመለሱ ሥራ የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ አስፈላጊው በጀት፣ የሎጀስቲክ እና አዲስ አበባ ሲደርሱ ወደ ትውልድ ቀዬዓቸው እስከሚጓዙ ድረስ የሚቆዩባቸው መጠለያዎች ዝግጁ እየተደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ዕቅዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ሳይዙ በመቅረታቸው በእስር ቤት የነበሩ ዜጎቿን ስትመልስ ቆይታለች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊትም 100 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ እስር ቤቶች ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት፣ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ወደ ሀገራቸው መልሳለች፡፡

ከ2009 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ባሉት ሶስት ዓመት ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።

በህወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በተሳሳተ መረጃ አማካኝነት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በጅቡቲ እና የመን በኩል አድርገው በእግራቸው እና በባህር ትራንስፖርት ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያዊያን በህገወጥ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንዲሰደዱ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጥናት ያስረዳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *