በእስር ላይ የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብትን  በሁለት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ አንስቷል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው ከቋሪት ወረዳ ተመርጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሪፖርታቸውን ለምክር ቤቱ በሚያቀርቡበት ወቅት ጠንካራ ጥያቄዎችን በማንሳት እና ትችቶችን በመሰንዘር የሚታወቁት አቶ ክርስቲያን ታደለ ከስድስት ወራት በፊት ታስረዋል፡፡

ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ላለፉት ስድስት ወራት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ክርስቲያን ታደለ በዛሬው ዕለት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል፡፡

ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከሁለት ወራት በፊት ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በተመሳሳይ በእስር ላይ ያሉ ሲሆን እስካሁን ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ፍርድ ቤትም ሳይቀርቡ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ካሳ ተሻገር በተመሳሳይ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ካሳለፍነው ጥቅምት ወር ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱ ይታወሳል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡

ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የነበረ ሲሆን አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በዚህ ጦርነት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ15 ቢሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተከሰተዉ ጦርነት 298 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ 3725 ትምህርት ቤቶች ደግሞ እንደተዘጉ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *