የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ከማሰር ሊቆጠቡ ይገባል ሲል የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ አሳሰበ
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ በሶማሌ ክልል የታሰረውን ጋዜጠኛ ሙህያዲን መሀመድ አብዱላሂን አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ከማሰር ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከአንድ ወር ገደማ በፊት የታሰረውን ጋዜጠኛ ሙህያዲን መሀመድ አብዱላሂን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ጠይቋል።
ሙክሲየዲን ሾው፤ በሚል የፌስ ቡክ ገፁ ላይ ዘገባዎችን እና አስተያየቶችን የሚጽፈው ሙህያዲን፤ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ፤ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚቴው አመልክቷል።
በመጋቢት 4 ቀን ሙህያዲን የኢትዮጵያን የጥላቻ ንግግር እና የሀሰት መረጃ ህግን በመጣስ እና የሀሰት ዜና እና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ክስ ተመስርቶበታል። የጋዜጠኛው የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ አምስት አመት እስራት ሊያስቀጣው ይችላል ሲል ሲፒጄ አስታውቋል።
ሙህያዲን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የካቲት 12 ቀን «ህዝቡን በፌስቡክ ገፁ ላይ በማነሳሳት» የተከሰሰ ሲሆን፤ሲፒጄ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 5 ቀን በጋዜጠኛው የፌስቡክ ገጽ አደረኩት ባለው ግምገማ የካቲት 11 ቀን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጉብኝት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጅግጅጋ ውስጥ የተዘጉ መንገዶችን የሚተች ልጥፍ ማጋራቱን አስታውቋል።
የጋዜጠኛውን ጉዳይ በተመለከተ ሲፒጄ ከክልሉ ባለስልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን አመልክቷል።