በዚህ ግምገማ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ ህወሃት፣ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት የአፍሪካ ህብረት በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጦርነቱ መቆሙ ይታወሳል፡፡
ይህ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን በስምምነቱ መሰረት ያልተፈጸሙ ጉዳዮች እንዳሉ በሁለቱም ወገኖች ሲነሳ ቆይቷል፡፡
አፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያ የተኩስ ማቆም ስምምነት አፈፃፀም ስትራቴጂካዊ ግምገማ እያካሄደ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋ አድርገዋል።
የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገፃቸው ባጋሩት መልእክት የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያ የተኩስ ማቆም ስምምነት አፈፃፀም ስትራቴጂካዊ ግምገማ እያካሄደ ነው ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ አለበት “ሲሉም ጌታቸው ተናግረዋል።
በዚህ መድረክም የመንግስት እና ህወሓት ተወካዮች ፣ የአፍሪካ ኅብረት ፓነል አባላት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ኢጋድ እና የአሜሪካ ታዛቢዎች በተገኙበት የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን እንደሚገመግሙ ተገልጿል።
አቶ ጌታቸው በዚሁ ፅሑፋቸውም በኢትዮጵያና በትግራይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አለበት ብለዋል።
በተያያዘ ጉዳይ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባዋጣው መግለጫ የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሀማር በአፍሪካ ህብረት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ግምገማ እንደሚሳተፉ አስታውቋል።
ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህ ጦርነት ለዓመታት በብድር እና በህዝብ ገንዘብ የተገነቡ መሰረተ ልማተቶችን እንዲወድም ያደረገ ሲሆን በአጠቃላይ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በሀገር ላይ እንዳደረሰ ተገልጿል።
ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ ተጎድተዋልም ተብሏል።
በዚህ ውስጥ ምክንያትም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ወደ ከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።
በዚህ ጦርነት የደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል ሆኗል።
በአጠቃላይ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ያስረዳል።