ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ከተላከ ቅባት እና ጥራጥሬ እህሎች 285 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች

ባለፉት ስድስት ወራት ከቅባትና ጥራጥሬ እህሎች የወጪ ንግድ 285 ነጥብ 53 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከቅባት እህሎች የወጪንግድ 109 ነጥብ 66ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን አፈጻጸሙም 109 በመቶ መሆኑን ሚኒሰቴሩ በስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ይህም ካምናው ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ26 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በስድስት ወራቱ በጥራጥሬ እህል የተገኘው ገቢ 176 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ77 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከቅባትና ጥራጥሬ እህሎች የወጪ ንግድ በድምሩ 285 ነጥብ 53 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የሰሊጥ እህል ላይ አለም አቀፍ የገበያ ፍላጎት መጨምሩ ፣ የጉሎ ፍሬ ለአለማቀፍ ገበያ ምርት በበቂ መቅረቡ ፣ላኪ ድርጅቶች በወቅቱ ወደ ውጭ መላክ የሚችሉበት የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ መደረጉ ከወጪ ግብይት የተገኘው ገቢ እንዲሻሻል ያደረጉ ምክንያቶች ናቸውም ተብሏል፡፡

ከቅባት እህሎች መዳረሻ ሀገራት መካከል እስራኤል፣የተባበሩት አረብ  ኢምሬት፣ሲንጋፖር፣ቪትናም እና አሜሪካ በቀዳሚነት ሲጠቀሱ ህንድ ፣ፓኪስታን፣ሲንጋፖር፣ቪትናም እና ኬንያ ደግሞ ከጥራጥሬ አህል መዳረሻዎች መካከል መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በእቅድ አፈጻጸሙ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከልም የፀጥታ ችግር ፣የሎጀስቲክ ወጪ መጨመር ፣የኮንትሮባንድ መስፋፋት ፣ የግብይት ህጎችን በአግባቡ ተገንዝቦ ተግባራዊ አለማድረግና የአቅም ዉስንነት ተጠቅሷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ከቆዳ ምርት እና ማዕድናት ንግድ የ200 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፀሐፊ እንዳለ ሰይፉ ባለፉት ሥድስት ወራት 124 ሚሊየን ዶላር ከቆዳ ምርቶች ሽያጭ ለማግኘት ታቅዶ መሰራቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ማሳካት የተቻለው 14 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ብቻ መሆኑን ተናግረው በግማሽ ዓመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

የቆዳ ዘርፉ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ የገቢ ማሽቆልቆል እንዳጋጠመውም አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት እጦትና ለዘርፉ የተሰጠው የትኩረት ማነስ ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያትም የቆዳ ፋብሪካዎች ከሥራ ውጭ እየሆኑ እንደሚገኙም ማህበሩ አስታውቋል።

የማዕድን ወጪ ንግድ ቅናሽ ያሳየ ሌላኛው ዘርፍ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 243 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ገቢ ግን 143 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2016 ዓም ወደ ውጭ ሀገራት ከተላከ ቡና 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት እቅድ ያላት ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ 570 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *