ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናበዊ ገንዘብ ወይም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ፍላጎት እየጨመረ ሲሆን በኢትዮጵያም አጀንዳ ከሆነ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትኛውንም ክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት እንዳልፈቀደ እና ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎችም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር፡፡
ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት መፈጸም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉ ኩባያዎች ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት እንዲደረግ ያልፈቀደች ሲሆን የዳታ ማዕከል ግንባታዎች እንዲካሄዱ ግን ስምምነቶችን በመፈራረም ላይ ነች፡፡
በዛሬው ዕለትም ዌስት ዳታ ማዕከል የተሰኘው ኩባንያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የቢትኮይን ግብይት እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ እና ቻይና ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከላቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የዳታ ማዕከላትን ለመገንባት ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ናቸው፡፡
ራክሲዎ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የዳታ ማዕከል ድርጅት በአዲስ አበባ በሚገኘው አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ገንብቶ ማጠናቀቁን ከሁለት ወር በፊት አስታውቋል፡፡
የክሊፕቶከረንሲ ፍላጎት እየጨመረ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ50 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ባለፉት ዓመታት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው የዓለም ምናባዊ ወይም ክሊፕቶከረንሲ መገበያያ ገንዘብ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በዚህ ምክንያት አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን ከ50 ሺህ ዶላር በላይ በመመንዘር ላይ ሲሆን ይህም ከሁለት ዓመታት በኋላ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ መሆን ችሏል።
የቢትኮይን ዋጋ በተከታታይ ጭማሪ ያሳየው አሜሪካ በምናባዊ መገበያያ ገንዘብ አክስዮን መሸጥ እና መግዛት እንደሚቻል ከፈቀደች በኋላ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ15 ሺህ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።
የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ ካሳለፍነው ወር ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ አድርጓል የተባለ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ150 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከሁለት ዓመት በፊት የምናባዊ ወይም ክሪፕዮከረንሲ ግብይቶች ተፈላጊነታቸው መጨመሩን ተከትሎ አንድ ቢትኮይን እስከ 60 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ነበር።