አሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ በኢትዮጵያ ቢሮውን እንደሚከፍት አስታወቀ

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአፍሪካና በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ውስጥ 30 ወኪል ቢሮዎችን እከፍታለሁ ብሏል፡፡

ሪቭኤክሴል እና አሜሪካን ሆስፒታል ዱባይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ስትራቴጂያዊ አጋርነትን እንደፈጠሩ አስታውቋል፡፡

አሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ በአፍሪካና ምስራቅ አውሮፓ 30 ወኪል ቢሮዎችን የመክፈት ዕቅዱን ያስጀመረ ሲሆን በዱባይ ጤና ባለስልጣን ዕውቅና ያላቸው 3 የህክምና ቱሪዝም ቢሮዎችን በናይጄርያ የተለያዩ ከተሞች ከፍቷል፡፡

በዓለምአቀፍ የንግድ መፍትሄዎች መሪ ተዋናይ የሆነው ሪቭኤክሴል ዓለምአቀፍ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራትን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት በማጠናከር ከአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ ጋር የለውጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነቱን በይፋ አሳውቋል፡፡

የአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ ይህንን ያረጋገጠው በ30 ወሳኝ የአፍሪካና የምስራቅ አውሮፓ ከተሞች የወኪል ቢሮዎች የማስፋፍያ ዕቅዱ አካል ሆኖ በናይጄርያ ሶስት ከተሞች የህክምና ቱሪዝም ወኪል ቢሮዎችን በመክፈት መጀመሩን ባሳወቀበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ጅማሮ የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች የዓለምአቀፍ የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጥረት አካል ነውም ተብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2024 በዱባይ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሚስተር ቡቲ አል ሙላ የመሐመድ እና ኦባይድ አል ሙላ ግሩፕ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ፣ ሸሪፍ በሻራ የመሐመድ እና ኦባይድ ግሩፕ በተጨማሪም የአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ  ዋና  ስራ አስፈጻሚ ፣ ዶ/ር ማርዋን አልሙላ በዱባይ የጤና ባለስልጣን የጤና ቁጥጥር ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፣ ቶኒ ፕሪንስዊል የሪቭኤክሴል ስራ አስፈፃሚ እና ታይባት መሀመድ በዱባይ የናይጄርያ ቆንስል ጀነራል ተገኝተዋል፡፡

ሪቭኤክሴል ዓለምአቀፍ የናይጄርያውን ጨምሮ ሌሎች ወኪል ቢሮዎችን ለማቋቋምና ለማስተዳደር በመላው አፍሪካ ያለውን ሰፊ ኔትዎርክ የሚጠቀም ሲሆን በአዲስ አበባም በተደጋጋሚ በመገኘት የዱባይ ኢኮኖሚና ቱሪዝምን  በመወከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ስራዎች ሲሰራ ነበር፡፡

የአሁኑም ስትራቴጅያዊ እርምጃ ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የጤና አገልግሎቶችን ለአፍሪካውያን ለማቅረብ ያለመ እንደሆነ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ቶኒ ፕሪንስዊል  እንዳሉት በሚቀጥሉት ወራት ሪቭኤክሴል በአፍሪካ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ለመድረስ ያለውን ቁርጠኝነት በማጠናከር በቀጣይ ኢትዮጵያ ዋና ዕቅዳቸው እንደሆነች ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ጥምረት ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም ሰው ተደራሽ ለማድረግ ያለንን የጋራ ራዕይ ያቀፈ ነው፡፡ የዚህ ጅምር አካል በመሆኔም ደስታ ይሰማኛል ›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ሸሪፍ በሻራ በበኩላቸው ‹‹ የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ከዋና ዋና ዓለምአቀፍ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ሆና እየሄደችበት ያለችበትን መንገድ አጠናክራ ቀጥላለች፡፡

በጤና አጠባበቅ ዘርፉ ላይ ዓለምአቀፍ ተዓማኒነቷ እያደገ መምጣቱ ያስደስተናል፡፡ እኛም ልዩ ልምዶችን በመያዝ የላቀ እና ዓለምአቀፍ የህክምና ቱሪስቶችን ለመሳብ በርካታ ስራዎች እያከናወንን እንገኛለን፡፡ 

የአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ፡ የተራቀቁ የህክምና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና በሕይወት ሳይንስ ከመላው አለም ካሉ ባለሙያዎች ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነው፡፡ ለታካሚዎቻችን ደህንነትና እርካታ ያለን ቁርጠኝነትም ዋናው መለያችን ነው›› ሲሉ በሻራ ገልጸዋል፡፡

ይህ የአሜሪካን ሆስፒታል-ዱባይ እና ሪቭኤክሴል መካከል ያለው አጋርነት የጤና አገልግሎት ክፍተቶችን በማጥበብ እና አማራጮችን በማስፋት ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገራት ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እርምጃ ነው ተብሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *