ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ከአራት ዓመት በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጡ

የትግራይ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ከአራት ዓመት በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጡ::

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ኢትዮጵያ ለዓመታት ወደ ጦርነት እንድተገባ የተገደደችበትን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ እሳቸው የሚመሩት የትግራይ ልዩ ሀይል እንዲያጠቃ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የተገደሉበት እና 28 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት የወደመበት ይህ ጦርነት ከአንድ ዓመት በፊት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ቆሟል፡፡

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በዛሬው ዕለት ከአራት ዓመት በኋላ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተዋል፡፡

ደብረጽዮን እና ሌሎች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በአዲስ አበባ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ጉዳይ እየመከሩ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስታውቋል።

በዚህ ውይይት ላይ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊዎች በተጨማሪ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መገኘታቸውን ጽ/ቤቱ የለጠፈው የምስል መረጃ ያሳያል።

የህወሓት ሊቀመንበር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌደራል መንግስት በህወሓት መካከል ከተፈረመው የፕሪቶሪያው የዘላቂ ሰላም ስምምነት በኋላ ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ይህ የፌደራል እና የክልል ኃላፊዎች የሚያደርጉት ስብሰባ በመልሶ ግንባታ እና በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ያተኩራል።

የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሻሻሎች መኖራቸውን ቢጠቅሱም አሁንም የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ሲያነሱ ይደመጣሉ።

የፌደራል መንግስት የሰላም ስምምነቱን መፈረም አንደኛ አመት መሰረት አድርጎ ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ስምምነቱን ከመፈጸም አንጻር “እግር የመጎተት አዝማሚያ” አለ የሚል ትችት መሰንዘሩ ይታወሳል።

የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ አለመፍታታቸውን በቅሬታ አንስቶ ነበር።

ስምምነቱን ሙሉ በመሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን በመግለጫው የጠቀሰው የፌደራል መንግስት የበለጠ መተማመን ለመፍጠር በማሰብ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የመወከል መብት እያለው ሳይወከል መቅረቱን ጠቅሷል።

ይህን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኘሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በፌደራል መንግስት በኩል ያልተፈጸሙ የስምምነት ነጥቦች መኖራቸውን በመጥቀስ ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *