ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር መክፈሏ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በመሻሻል ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመንግስታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሌት “ህገ መንግስት ጋር ተያይዞ ከአማራ ክልል ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፤ ስራውን እየሰራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ህዝብ በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት ምክንያት ተንቀሳቅሶ መስራት፣ ሀብት ማፍራት ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች እንዳይፈቱ አድርጓል የሚል ጥያቄ አላቸው፡፡

በዚህም መሰረት የአማራ ህዝብ ይህ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ሲዘጋጅ እና ሲጸድቅ በቂ ውይይት እንዳልተደረገበት እንዲሁም የአማራ ህዝብን አግላይ ነው በሚል ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

ለአብነትም የአማራ ክልል ወሰን አከላለል ትክክል አይደለም፣ በርካታ የክልሉ መሬቶች እና ሀብቶች ወደ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለ በቂ ውይይት ተወስደዋል የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት ከሚነሱት ጥያዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት “የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ለአንድ ክልል ብለን አናሻሽልም“ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ መሻሻል ዙሪያ ለተነሳው ጥያቄ “ሕገ መንግሥቱ እኛ ስንለቅ አብሮ የሚቀደድ ሕገ መንግሥት እንዳይኾን ቅድሚያ ብንመክር ይሻላል በሚል እየሠራን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የሰጡበት ጉዳይ መንግስታቸው ባለፉት ስድስት ወራት 270 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ አቅዶ 265 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ከታጠቁ ሀይሎች ጋር ለምን የቀጥታ የሰላም ድርድር አይጀመረም? በሚል ለቀረበው ጥያቄም መንግስት ታጣቂዎች የጦር መሳሪያቸውን ካስቀመጡ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሳላቸው ጥያቄ ኢትዮጵያ እንዴት እዳዋን መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ልትካተት ቻለች?  የሚለው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ኢትዮጵያ እዳዋን እንዳትከፍል ያደረጋት ምንም አይነት ችግር የለባትም ዋነኛው ችግር የሆነባት ብድር ሳይሆን አራጣ ነው ብለዋል።

አራጣ ማለት የተበደሩትን ገንዘብ በአብላጫ ጨምሮ መክፈል ሲሆን ችግር የሆነውም የብድሩ ገንዘብ የታሰበውን ስራ ሳይሰራ መመለስ አለመቻሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ 2011 እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ መክፈሏን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ መክፈል አቅቷታል የተባለው 33 ሚሊየን ዶላር የአየር መንገዳችን የሁለት ቀን ገቢ ነው ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ካለባት 28 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ክምችት ላይ 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ለማን እንደከፈለች ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላብራሩም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በፈረንጆቹ 2014 የ1 ቢሊዮን ዩሮ ከዩሮ ቦንድ ገዝቶ የነበረ ሲሆን የዚህ ብድር መክፈያ ጊዜን ከሁለት ወራት በፊት አሳልፋለች በሚል ከጋና እና ዛምቢያ ጋር እዳቸውን መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ተርታ ተመድባለች፡፡

ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ የገዛችውን ብድር ለመክፈል በወር 33 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል ግዴታ ያለባት ቢሆንም አበዳሪዎች የኢትዮጵያን የእዳ መክፈያ ጊዜ እንዲያሸጋሽጉ ያቀረበችው ጥያቄ ሲመለስ መክፈል እንደምትጀምር  የገንዘብ ሚኒስቴር መናገሩ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *