ታሪካዊው የኢትዮጵያ ቅርስ አል ነጃሺ መስጅድ በትግራይ ክልል የሚገኝ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ወቅት በከባድ መሳሪያ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ቱርክ ይህንን ታሪካዊ የእስልመና ቅርስ ለማደስ ለኢትዮጶያ መንግስት ጥያቄ እንዳቀረበች የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ እና የትግራይ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ቅርሱ በሚታደስበት ሁኔታ ከቱርክ የቀረበውን ጥያቄ መቀበላቸው ተገልጿል፡፡
ቅርሱ በሚታደስበት ሁኔታም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል የተባለ ሲሆን የቱርክ ቅርስ ጥገና ባለሙያዎች ወደ ቦታው አምርተው ምልከታ መጀመራቸውን የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ተናግረዋል፡፡
ለቅርሱ እድሳት የሚያስፈልገው በጀት ምን ያህል እንደሆነ እና ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
ለሁለት ዓመት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አል ነጃሺ መስጂድ በ2013 ዓ.ም ላይ በከባድ የጦር መሳሪያ የተመታ ሲሆን እስካሁን ለጥቃቱ ሀላፊነት የወሰደ አካል የለም፡፡
በቅርሱ ውስጥ የነበሩ ንብረቶች በኤርትራ ወታደሮች ተዘርፏል የተባለ ሲሆን ቅርሱ ከጦርነቱ በፊት በኢትዮጵያ ከሚጎበኙ ቦታዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በሚባሉት ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በተካሄደው የሁለት ዓመት ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደተገደሉ ሲገለጽ ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ንብረትም እንደወደመ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በጦርነቱ ለዓመታት በመንግስት ወጪ እና በብድር በተገኘ ገንዘብ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የወደሙ ሲሆን ክልሎቹን ወደ ነበሩበት ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የፌደራል መንግስት እና ህወሃት ታጣቂዎች መካከል የተካሄደው ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ መቆሙ ይታወሳል፡፡