ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ከሆነችው ባህርዳር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው መራዊ ከተማ ከሰሞኑ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
በዚህ ውጊያ ምክንያት የፋኖ ታጣቂዎች የመራዊ ከተማን ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ለቀው መሄዳቸውን ተከትሎ ወደ ከተማው የገባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ50 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችን እንደገደሉ ቢቢሲ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ዘግቧል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት ከሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነዋሪዎቹን ከመንገድ ላይ እና መኖሪያ ቤታቸው በማሰባሰብ ገድለዋቸዋል፡፡
በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች በተለይም የገጠር አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ሲያዙ ከተሞች ደግሞ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር፡፡
ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን በሁሉም የክልሉ ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው፡፡
አሜሪካም በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ እንዳሳሰባት ያስታወቀች ሲሆን ጉዳዩ በድርድር እና ውይይት እንዲፈታም ጠይቃለች፡፡
በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲን ወክለው የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑት ውስጥ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እና ክርስቲያን ታደለ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ይታወሳል።
በአጠቃላይ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር በተያያዘ በባህር ዳር ፣ በጎንደር እና በኮምቦልቻ ከተሞች 706 ሰዎች መታሰራውን የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ጌዴዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን እንደማይደግፍ ገልጾ በአማራ ክልል የተጣለው አዋጅ ስድስት ወር ሳይሞላው እንደሚነሳ ከመንግስት ቃል እንደተገባለት መናገሩ ይታወሳል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት እንደሚገድብ እና በክልሉ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስራዎቹን ተዘዋውሮ መስራት እንዳልቻለም ህብረቱ አስታውቋል፡፡
አሜሪካ፣ አፍሪካ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ጦርነቶች እንዲቆሙ ፣ የድሮን ጥቃቶች እንዲቆሙ እና ልዩነቶቻቸውንም በንግግር እንዲፈቱ አሳስበው ነበር፡፡