የኢትዮጵያ እና አረብ ኢምሬት የጦር ጄቶች የጋራ አየር ትርኢት አካሄዱ

የኢትዮጵያ አየር ሀይል የተመሰረተበትን 88ኛ ዓመት በማክበር ላይ ስትሆን በዛሬው ዕለት ከተባበሩት አረብ ኢምሬት የጦር ጄቶች ጋር በመሆን የአየር ላይ ትርዒት አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ የጦር አውሮፕላኖች ትርዒት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የጦር አውሮፕላኖች ያካሄዱት የአየር ላይ ትርዒት “የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል፡፡

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ወታደራዊ አታሼዎች ባሳለፍነው ሳምንት ቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያን አየር ሀይል ዋና ማዘዣን የጎበኙ ሲሆን በዛሬው በዓል ላይም ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ1928 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአፍሪካ ካሉ አየር ሀይሎች በእድሜ ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ወታደራዊ ትርዒቶችን በአደባባይ ላይ ማክበር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት 2010 ወዲህ ብቻ በዓመት ቢያንስ አራት ጊዜ ይዘጋጃል፡፡

ከሶስት ዓመት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ አቅራቢያ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በህወሃት ታጣቂዎች መመታቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባሳለፍነው ዓመት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጦርነት ወቅት የተባበሩት አረብ ኢምሬት ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ድሮንን ጨምሮ የጦር መሳሪያዊችን ድጋፍ እንዳደረገች ይገለጻል፡፡

ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት አረብ ኢምሬት አሁንም ለፌደራል መንግስት የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንድታቆም ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሀገሪቱ በምታቀርበው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ምክንያት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በንጹሃን ዜጎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የድሮን ጥቃት እያደረሱ እንደሆነ እነዚህ ተቋማት ከሰዋል፡፡

ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮም በአማራ ክልል ሌላ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመዋጋት ላይ ናቸው፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎችን አሁንም ተቆጣጥረው እንደያዙ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ታጣቂዎቹን ለመደምሰስ በተለያዩ ግንባሮች ውጊያ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋና መንገድ ከተዘጋ ሁለት ሳምንት ያለፈው ሲሆን በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *