ብሔራዊ ሎተሪ የ8 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ እድለኛ እንደጠፋበት ገለጸ

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር በየጊዜው ለሽፓጭ ከሚያውላቸው የእድል ሎተሪዎች መካከል የእንቁጣጣሽ ሎተሪ አንዱ ነው።

20 ሚሊዮን ብር የሚያሸልመው ይህ እጣ ባሳለፍነው ጷግሜ 2015 ዓም እጣው የወጣ ሲሆን 1820259 ደግሞ የመጀመሪያ እድለኛ ቁጥር እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ንዋይ ለዓልዐይን እንዳሉት “ባሳለፍነው ጷግሜ ላይ ከወጣው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ ከሶስት እጣ አሸናፊ በስተቀር የሁለት እጣ አሸናፊዎች እስካሁን አልመጡም” ብለዋል።

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድሩ የሁለት እጣ እድለኞች ማለትም የስምንት ሚሊዮን ብር አሸናፊዎች እስከ ቀጣዩ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ካልመጡ ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ ይሆናልም ብለዋል።

20 ሚሊዮን ብር ከሚያሸልመው እጣ ቁጥር ውስጥ እስካሁን በመተሀራ ከተማ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በወዛደርነት እና በሹፌርነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ጓደኛሞች 12 ሚሊዮን ብሩን ወስደዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ 8 ሚሊዮን ብር የሚያሸልም ሁለት እጣዎች ያለው ወይም ያላት ሰው እስካሁን አልመጡም ሲሉም አክለዋል።

ሎተሪ እጣ ቆርጠው ቲኬቱን ደግመው እጣው ስለመውጣቱ እና አለመውጣቱን የማያረጋግጡ የሎተሪ ደንበኞች ስለሚኖሩ እጃቸው ላይ ያለውን ሎተሪ በድጋሚ እንዲያስተያዩም አቶ ቴድሮስ አሳስበዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት አንድ የ20 ሚሊዮን ብር ሎተሪ ተሸላሚ ግለሰብ የሽልማት ጊዜው ሊያበቃ አምስት ቀናት ብቻ ሲቀረው መጥቶ እጁ ላይ በተገኘው ሶስት ሎተሪዎች መሰረት 16 ሚሊዮን ብሩን መውሰዱ ይታወሳል።

ሎተሪው ወጥቶ ሽልማታቸውን የማይወስዱ ሰዎች አጋጥሞ ያውቃል? በሚል ላነሳነው ጥያቄም ” በተለይ አነስተኛ ሽልማት የሚያስገኙ እጣ የወጣላቸው ሰዎች የማይመጡበት እና ገንዘቡም ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር ሕግ መሰረት እጣ የወጣላቸው እድለኞች እጃቸው ላይ ያለውን ሎተሪ ይዘው በስድስት ወራት ሽልማታቸውን መውሰድ የሚችሉ ሲሆን ስድስት ወራት ካለፈ ግን ገንዘቡ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ይደረጋል ይላል።

ከ60 ዓመት በፊት ስራ የጀመረው ብሔራዊ ሎተሪ የሎተሪ እድሎችን በቁጥር እና በሽልማት መጠን በየጊዜው እያሳደገ ይገኛል።

አስተዳድሩ አሁን ላይ 14 አይነት የሎተሪ እድል መሞከሪያ እጣዎች ያሉት ሲሆን አድማስ ድጅታል፣ ቶምቦላ፣ ዝሆን፣ እንቁጣጣሽ፣ ትንሳኤ፣ የገና ስጦታ፣ ልዩ፣ ቢንጎ እና ፈጣን ሎተሪዎች ዋነኞቹ ናቸው።

አሁን ላይ ተቋሙ ከ15 እስከ ሁለት ወራት የሚቆዩ የሎተሪ አሸናፊ እጣዎች ያሉት ሲሆን ለባለ እድለኞች እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ በመሸለም ላይ ይገኛል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *