የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል አቋርጦት የነበረውን በረራ እንደሚጀምር ገለጸ፡፡

ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ እና ያለተጠበቀ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ 47ኛ ቀኑን ይዟል።

ከሁለቱም ወገን 15 ሺህ ገደማ ሰዎች የተገደሉበት ይህ ጦርነት እንዲቆም በርካቶች ሲያሳስቡ ቢቆዩም ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን አየር መንገዶች ወደ እስራኤል ሲያደርጉት የነበረውን በረራ አቋርጠው ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን በረራ ዳግም እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ አክሎም በሳምንት አምስት ቀናት ከአዲስ አበባ-ቴልአቪቭ ከተማ የቀጥታ በረራውን እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የደርሶ መልስ ትራንስፖርት አገልግሎቱን በበረራ መስመር ኢት 404 እና 405 አውሮፕላኖቹ  እንደሚሰጥ የገለጸው አየር መንገዱ ሁሉንም የሳምንቱ ቀናት አገልግሎቱን እሰጣለሁም ብሏል፡፡

ከዚህ በፊት ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ አልያም ከአዲስ አበባ ቴልአቪቭ ለመብረር የጉዞ ቲኬት የገዙ ደንበኞች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የበረራ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡


እንዲሁም የቲኬት ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ያለምንም ቅጣት እንመልሳለን ያለው አየር መንገዱ ደንበኞች የበረራቸውን ጊዜ ማራዘም ከፈለጉም እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ቀናት ድረስ ማራዘም ይችላሉ ሲልም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ሳምንት ከቦይንግ እና ኤርባስ የአቪዬሽን ተቋማት 78 አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቱ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *