የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ጃል መሮ ፊት ለፊት ተገናኙ

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪው ጃል መሮ ፊት ለፊት መገናኘታቸው ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ የሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር መጀመራቸው ተሰምቷል።

ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ የሰላም ንግግሩ ጥቂት ቀናትን እንዳስቆጠረና ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ የጦር አባላት ተወካዮች በተገኙበት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ዛንዚባር የተካሄደውን ድርድር የምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ኬንያ አስተባባሪ እና አሸማጋይ ሚና መውሰዳቸው ይታወሳል።

አሁን የተጀመረውን ንግግር ማን እንደሚያደራድር ግልጽ ባይሆንም፣ ኢጋድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሚና ሳያስቀጥል እንዳልቀረ ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ አዲስ ስታንዳርድ ሁለት የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በሰላም ውይይቱ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ኩምሳ ደሪባ / ጃል ማሮ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።

ጃል ማሮ በሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች አመቻችነት በምዕራብ ኦሮምያ ከሚገኝ ጫካ ወደ አቅራቢያው ወደሚገኘው የደንቢዶሎ አውሮፕለን ማረፊያ እንዲበር ከተደረገ ለኃላ ወደ ድርድሩ ቦታ በተዘጋጀለት ሂሊኮፕተር መጓዙም ተነግሯል።

በዚህም ጃል ማሮ ለመጀመሪያ ግዜ ከፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለውውይት መቀመጡ ተገልጿል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ባለፉት  ሳምንታት የፌደራል መንግሥት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይቱ ተካሂዷል።

ውይይቱ ውጤታማ ስለነበር እና በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ትላንት ከጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ በታንዛኒያ ዳሬሰላም መጀመሩን ተነግሯል።

ከሁለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው በቀደመው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ሥነ ስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል።

ውይይቱን በማመቻቸት ረገድ ኢጋድ ትልቁን ሚና መጫወቱን ፤ የኢጋዱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዋና አወያይ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና ስለ ፌደራል መንግስት እና ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ውይይት እስካሁን ስለድርድሩ የተባለ ነገር የለም።

ከስድስት ወራት በፊት በታንዛኒያ ዛንዚባር በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ድርድር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት ባለመቻሉ ያለውጤት መበተኑ አይዘነጋም።

የኦሮሚያ ነጻነት ሰራዊት በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች፣ እገታ፣ ዘረፋ እና የከፋ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚያደርግ በተለያዩ ጉዜያት የወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡

ይህ የታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ ሲገለጽ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች የቡድኑን ይዞታዎች ለማስለቀቅ በርካታ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወታደራዊ ክንፍ ተደርጎ የሚወሰደው ይህ የታጣቂ ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጇል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት እና ጦርነት የተከሰቱ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በአማራ ክልል ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመዋጋት ላይ ሲሆኑ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም በፋኖ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ከነዋሪዎች ሰምተናል፡፡

በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን ካሳለፍነው ሀምሌ ጀምሮም የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡

አሁን ላይ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ጎጃም እና ጎንደር ዞኖች የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከባድ ውጊያ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማን ለመቆጣጠር የጨበጣ ውጊያ በከተማዋ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡  

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *