በአማራ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ 300 ዜጎች በታጣቂዎች ተገደሉ

የኦሮሚያ እና አማራ ክልል የሚዋሰኑበት የሰሜን ሸዋ ዞን ስራ የሚገኙ ወረዳዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡

ደራ የተሰኘው ወረዳ ደግሞ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስበት አካባቢ ሲሆን በሶስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 300 ንጹሃን ዜጎች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገልጿል፡፡

ኦነግ ሸኔ ከሶስት ዓመት በፊት  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጆ መንግስት ይህን የሽብር ቡድን ለማጥፋት እርምጃ እየወሰድኩ ነው ቢልም ቡድኑ ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል፡፡

አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የደራ ወረዳ ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንዳሉት “በሦስት ሳምንታ ውስጥ ከ300 በላይ ንጹሐን በሸኔ ታጣቂዎች ተገድለዋል።” ያሉ ሲሆን፤ ይህ እርሳቸው ያላቸው ትክክለኛ መረጃ እንደሆነ በመግለጽ፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊያሻቅብ እንደሚችል እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኹኔታውን በቅርበት እየተከታሉ መሆኑን ያስረዱት እኚሁ ታማኝ ምንጭ፤ ከ80 በላይ የሟቾች ሥም ዝርዝር እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ሌሎች የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው ጥቃቱ የተከፈተው ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ መሆኑን ገልጸው፤ ጥቃቱ አሁንም እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡

በደራ ወረዳ ስር ያሉ ከ20 በላይ ቀበሌዎች በዚሁ የሽብር ቡድን ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆኑም የተገለጸ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

በታጣቂ ቡድኑ የታገቱ ሰዎች እስከ 1 ሚሊዮን ብር እየተጠየቀባቸው እንደነበርና የከፈሉት እደተለቀቁ የገለጹት የዓይን እማኞቹ፤ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የተጠየቁትን ገንዝብ በመክፈል ያልቻሉ ታጋቾች ተገድለዋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ደራ ወረዳን ጨምሮ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎች ንጹሃንን እየገደሉ እና እያገቱ ስለመሆኑ ጥቆማ እንደደረሰው እና ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን እና የክልሉ አስተዳድር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከአዲስ አበባ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው ዱከም ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሀይል እና የኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ዋዜማ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ የክልሉን ቦታዎች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *