በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ተመድ አስታወቀ

በኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት የጸጥታ ሀይሎች እና በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ ምክንያት፤ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያስችል ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪ ገለጹ።

የድርጅቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሪሙ በኢትዮጵያ ስላለው ኹኔታ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ፤ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች ምክንያት በአገሪቱ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች የመፈጸም ኹኔታዎች እንዲኖሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

“በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ስላሉት ወንጀሎች የተመለከቱ የሚደርሱን ሪፖርቶች እጅግ የሚረብሹ ናቸው” ያሉት ልዩ አማካሪዋ፤ “በአፋጣኝ ኹኔታውን ለመከላከል እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።” ብለዋል።

አክለውም፤ “እየደረሱን ካሉ ሪፖርቶች መካከል የአንድ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ግድያ እንደተፈጸመባቸው፣ ቤተሰቦች በሚወዷቸው ወገኖቻቸው ላይ የሚፈጸምን አሰቃቂ ተግባር እንዲመለከቱ ስለመደረጉ በተጨማሪም ሙሉ መንደር ተፈናቅሎ ቤቱን ጥሎ እንዲሰደድ ስለመደረጉ የሚገልጹ ይገኙበታል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

በአገሪቱ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ሌሎች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ከአሁኑ መከላከል እንደሚያስፈልግም ልዩ አማካሪዋ አሳስበዋል።

“የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ሚሊሻዎች በትግራይ ሴቶች ላይ የሚፈጽሙት አስከፊ ወንጀል፣ አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃት እንደቀጠለ ነው።” ሲሉ የገለጹት ልዩ አማካሪዋ፤ “በአማራ ክልል የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ አስከፊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ለመሆናቸው አሳማኝ ማስረጃዎች አሉም” ብለዋል፡፡

የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ “በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው፡፡” ሲል መግለጹን ልዩ አማካሪዋ በአብነት አስቀምጠዋል፡፡

በመሆኑም፤ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ባስቸኳይ እንዲቆሙም እና አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት አሊስ ዋይሪሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈጸም ይችላል በሚል የወጣው የተመድ ሪፖርትን እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ “ዓለም እንዳሉት የተመድ ሪፖርት በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ እና ትክክለኛ ሪፖርት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *