የኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም አሠሪዎች ፌዴሬሽን እንደገለጸው በኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም ስራ በየጊዜው እየተዳከመ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት ለቪኦኤ እንዳሉት የሆቴል እና ቱሪዝም ቢዝነስ በዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመልሷል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያም የሆቴል ኢንዱስትሪ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት እንዲያገግም ለመንግስት በቀረቡለት ምክረ ሀሳቦች መሰረት እርምጃ መውሰዱ ዘርፉን ከባሰ ጉዳት ታድጎታል ብለዋል።
የኮቪድ ፕሮቶኮል በሚል ወደ ስራ የተተገበረው አሰራር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ሆቴሎችን ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ግን በየጊዜው እየተዳከመ እና በርካታ የሆቴል ቢዝነስ ባለሀብቶች እና ባለሙያዎች ወደ ሌላ ቢዝነስ እየገቡ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የሆቴል ኢንዱስትሪውን ጎድቶት ቆይቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁን ደግሞ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልለፐች ያለው ጦርነት እና የጸጥታ ችግር ተጨማሪ ጉዳት በማድረስ ላይ ነውም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ሁኔታ ባንኮች የሆቴል ባለቤቶች የወሰዱትን ብድር እንዲከፍሉ ጫና በማድረግ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
መንግስት የሆቴል ኢንዱስትሪው ወደ ተባባሰ ችግር ከመግባቱ በፊት የባንኮችን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ ግፊት እንዲያደርግም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡
ባንኮች ለሆቴል ኢንዱስትሪ የሚሰጡት ብድር የመክፈያ ጊዜ አጭር መሆኑ፣ በጦርነቱ ሆቴሎች ኢላማ መደረጋቸው እና በጦርነቱ ምክንያት ሆቴሎች ከስራ ውጪ መሆናቸው ዘርፉን ክፉኛ እየጎዱት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ እድገት ጥሩ የሚባል ነው የሚሉት ፕሬዘዳንቱ አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ግንባታቸው መቆሙን በአንድ ዓመት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
እንደ ፍትህ ወልደሰንበት ገለጻ “የነዚህ ሆቴሎች ግንባታ የቆመው በውጭ ምንዛሬ እና በባለሃብቶች ፍላጎት ማጣት ምክንያት ነው”።