የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያ ወደ ሀገር አቀፍ ግጭት እያመራች ነዉ ሲል አሳዉቋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለዉም ግጭት ተበራክቷል ያለው ተመድ የግጭቶች መበራከት ኢትዮጵያን ወደ ሀገር አቀፍ መጠነ ሰፊ ግጭት ሊወስዳት ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል ያለዉን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የጅምላ እስር እና እንግልት እየተፈጸመ እንደሆነም አስታውቋል።
ድርጅቱ በመግለጫው አክሎም በክልሉ ፤ በመንግስት ቢያንስ አንድ ጊዜ የሰዉ አልባ አዉሮፕላን ጥቃት መፈጸሙን የደረሱኝ ሪፖርቶች ያመለክታሉ ሲልም ጠቅሷል።
በአማራ ክልል በርከታ ከተሞችም ከሲቪል አስተዳደር ዉጪ በመሆን በወታደራዊ ስርዓት ስር ወድቀዋል ተብሏል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን ጦርነት ተከይሎ ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ተከትሎ ክልሉ በወታደራዊ አመራር እየተመራ ይገኛል።
በዚህ ምክንያትም የክልሉ የጸጥታ ሁኔታም ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተመድ አስታውቋል።
ተመድን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰባቸው በመናገር ላይ ናቸው።
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረትም በኢትዮጵያ በአማራ እና ኦሮሚያ ያለው የጸጥታ ችግር በውይይት እንዲፈታ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።